Fana: At a Speed of Life!

ሁለተኛውን ዙር የኮቪድ 19 ክትባት ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው – ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁለተኛውን ዙር የኮሮና ቫይረስ የክትባት መርሃ ግብር ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰሃረላ አብዱላሂ አስታወቁ፡፡

በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ፍቃድ የተሰጣቸው አስትራዜኒካ እና የሲኖ ፋርም ክትባቶችን ከመጋቢት መጀመሪያ ጀምሮ የመጀመሪያ ዙር ክትባት መሰጠቱ ይታወሳል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዋ 5 ነጥብ 5 ሚሊየን መጠን የያዘ ክትባት ከለጋሽ ሃገራት ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡

እስከ ህዳር 2014 ዓ.ም ድረስ 20 ሚሊየን ክትባት ወደ ኢትዮጵያ የማስገባት እቅድ ተይዞም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ቅድሚያ የሚሰጣቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ክትባቱን እያገኙ ሲሆን የጤና ሚኒስቴር በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረትም እስካሁን 470 ሺህ ዜጎች ክትባቱን ወስደዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ በዕድሜ ከፍ ባለው የህብረተሰብ በኩል የመከተብ ፍላጎት ቢኖርም አንዳንድ የተዛቡ ግንዛቤዎች በክትባቱ ሂደት ላይ አሉታዊ ጫና እየፈጠሩ ነው።

በተለይም ክትባቱን ከእምነት ጋር ማያያዝ ሌላው ፈተና መሆኑን ጠቁመው፣ ለዚህም ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን ችግሩን ለመፍታት የሚያግዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ አስረድተዋል።

የአስትራዜኒካ ክትባት ለደም መርጋትና ሌሎች የጤና እክሎች እንደሚዳርግ ተደርጎ በአንዳንድ የመገናኛ ብዙኀን መሰራጨቱን ጠቁመው፣ በኢትዮጵያ ክትባቱን ከወሰዱ ሰዎች እስካሁን ያጋጠመ የጤና እክል አለመኖሩን አረጋግጠዋል።

ክትባቱ በአሁኑ ወቅት ተጋላጭ ናቸው ተብለው ለተለዩ የጤና ባለሙያዎች፣ ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጎችና ዕድሜያቸው ከ50 እስከ 60 ሆኖ ተጓዳኝ ህመም ላለባቸው ሰዎች ቅድሚያ በመስጠት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ በአንዳንድ ቦታዎች ከተቀመጠው የዕድሜ ገደብ ውጪ ክትባቱ እየተሰጠ መሆኑን ለእኛም በሚደርሱ ጥቆማዎች አሉ ያሉ ሲሆን ሚኒስቴሩ እርምጃ ይወስዳል ማለታቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.