Fana: At a Speed of Life!

የህዝቡን ማህበራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ ኢዜማ ይሰራል – ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የህዝቡን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን በመመለስ ማህበራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ እንደሚሠራ የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

ፕሮፌሰሩ በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዙሪያ ከአባላትና ደጋፊዎቻቸው ጋር ዛሬ  በአርባምንጭ ከተማ ተወያይተዋል።

የሀገሪቱ ፖለቲካ በዘር ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች በህዝቡ ላይ እንዲደርስ ምክንያት መሆናቸውን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከዘርና ሃይኖማት መነጠል አለበት ያሉት ፕሮፌሰሩ ፓርቲያቸው የሚያራምደው የዜግነት ፖለቲካ የኢትዮጵያን ህዝብ አብሮነትና መቻቻልን የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ጥቂት ሰዎች በልጽገው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ የበይ ተመልካች ሆኖ ለዘመናት መቆየቱን ጠቅሰው የህዝቡን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በፍትሃዊ መንገድ በመመለስ ማህበራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ ኢዜማ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ፓርቲው የፌደራል ስርዓቱን ሙሉ በሙሉ እንደሚያምንበት አመልክተው ሆኖም ዜጎች በተወካይ ሳይሆን ቀጥታ የሚያስተዳድሯቸውን አካላት በመምረጥ የሚተዳደሩበት መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ለህዝቦቿ በቅታ የምትተርፍ ብትሆንም የአስተዳደር በደልና ስግብግብነት ወደ ኋላ እንዲጎተት አድርጎታል ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ ፓርቲና መንግስት የተደበላለቀ በመሆኑ መንግስት የፓርቲው አገልጋይ ሆኖ ቆይቷል ሲሉም ገልጸዋል።

የዘንድሮው ምርጫ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ዴሞክራሲያዊና እውነተኛ ምርጫ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰው ኢዜማ ካሸነፈ የፓርቲና መንግስት ድርሻ እንዲለይ ከማድረግ ባለፈ ተመራጩ በቀጥታ ለመረጠው ህዝብ ተጠያቂ የሚሆንበት ስርዓት ይፈጠራልም ብለዋል።

ሁሉም የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎችም ከምርጫ ህግና ስነ-ምግባር ደንብ ሳይወጡ የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች በትዕግስት በማለፍ ለውጤታማነት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በጋሞ ዞን ጨንቻ ወረዳ የኢዜማ አባል አቶ ነጋ ባልቻ በበኩላቸው፤ የዘንድሮ ምርጫ ያሉብንን ችግሮች በመሰረታዊነት መፍታት የሚያስችል መሪ የሚመጣበት ይሆናል ብለዋል።

በሀገሪቱ ህዝቡ ያጋጠመውን የኑሮ ውድነትና የፀጥታ ችግር ሊቃለል የሚቻለው በኢዜማ ብቻ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ ከአርባ ምንጭ ከተማ ወይዘሮ አማረች ክልኮ ናቸው።

የትምህርት ስርዓቱም በመዳከሙ የሚወጡ ምሩቃን ብቁ ካለመሆናቸው በላይ የስራ አጥ ቁጥር በእጅጉ እየተስፋፋ በመሆኑ ብቁ ዜጋ ለማፍራት የትምህርት ፖሊሲው እንዲሻሻል ኢዜማ መስራት አለበት ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.