Fana: At a Speed of Life!

ሠራተኞችን ከአንድ ተቋም ወደ ሌላ ተቋም አዘዋውሮ ማሠራት የሚያስችል አሠራር ተግባራዊ ሊደረግ ነው

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 12 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)በአዲስ አበባ ከተማ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚሰጠውን አገልግሎት ተደራሽ እና ቀልጣፋ ለማድረግ ሠራተኞችን ከአንድ ተቋም ወደ ሌላ ተቋም አዘዋውሮ ማሠራት የሚያስችል አሠራር ተግባራዊ እንደሚያደርግ የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ኃይሉ ሉሌ ÷ ከፍተኛ የአገልግሎት እና የመልካም አስተዳደር ችግር በሚታይባቸው ተቋማት ላይ የሠራተኞች ዝውውር በማድረግ ተደራሽ እና ቀልጣፋ  አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል መመሪያ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

በከተማዋ ከማዕከል ጀምሮ በክፍለ ከተማ እና ወረዳ ድረስ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እና የሕዝብ እንግልት ይበዛባቸዋል በተባሉ 11 ተቋም ጥሩ ሥነ-ምግባር፣ ችግር ፈቺ፣ የአገልጋይነት መንፈስ እና ተነሳሽነት እንዲሁም ጥሩ አፈጻጸም ያላቸውን ባለሙያዎች በተቀመጠው መስፈርት የመመደብ ሥራ እንደሚካሄድም ነው የገለጹት ።

በሙከራ  ደረጃ በመሬት እና መሬት ነክ ተቋማት ላይ ተግባራዊ ተደርጓል ያሉት አቶ ኃይሉ÷ በቅርቡም በመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።

በቀጣይም በጥናት እና የህብረተሰቡ የአገልግሎት ፍላጎት ላይ በመመሥረት በሌሎች ተቋማት ላይ ተግባራዊ  እንደሚደረግ አቶ ኃይሉ አብራርተዋል።

የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሳለጥ የሠራተኞችን እውቀት እና ክህሎት ከማብቃት ባለፈ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥርዓት በመዘርጋት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

አዲሱ አሠራር የሚስተዋለውን የአገልግሎት እንግልት በጊዜያዊነት ለመቅረፍ የተዘጋጀ አሠራር መሆኑን ያሉት ኃላፊው አስረድተዋል።

ይህ አሠራር ደሞዝ የመቀነስም ሆነ የመጨመር ዓላማ እንደሌለው የገለጹት አቶ ኃይሉ÷  ሠራተኞች ባላቸው የትምህርት ዝግጅት እና የሥራ ልምድ መሠረት በገለልተኛ አካል ተገምግሞ የመመደብ ሥራ እንደሚሠራ መግለጻቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬተሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፦https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.