በደቡባዊ አፍሪካ 45 ሚሊየን ሰዎች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸው ተነገረ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ፕሮግራም በደቡባዊ አፍሪካ 45 ሚሊየን ሰዎች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን አስታወቀ።
ለምግብ እጥረት ከተጋለጡት መካከል አብዛኛዎቹ ህጻናትና ሴቶች መሆናቸውም ተገልጿል።
በደቡባዊ የአፍሪካ ሃገራት የተከሰተው ድርቅ፣ የጎርፍ አደጋ፣ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር እድገት እና ዝቅተኛ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለምግብ እጥረቱ ምክንያት መሆኑም ነው የተነገረው።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም የደቡባዊ አፍሪካ ሃገራት ዳይሬክተር ሎላ ካስትሮ ሁኔታው ከዚህ ቀደም ያልታየና ወደ ከፋ ደረጃ ሊያመራ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ድርጅቱ ለምግብ እጥረት ለተጋለጡ ሰዎች ከሚያስፈልገው 489 ሚሊየን ዶላር ውስጥ እስካሁን 205 ሚሊየን ዶላር ብቻ መሰብሰብ መቻሉንም ገልጸዋል።
ከዚህ አንጻርም አስፈላጊውን ገንዘብ ማግኘት ካልተቻለ ሁሉንም ሳይሆን ለከፋ የምግብ እጥረት የተዳረጉትን ብቻ በመደገፍ የተወሰኑትን ለመታደግ እንገደዳለንም ብለዋል ዳይሬክተሯ።
አሁን ላይ በአካባቢው ሃገራት የተከሰተው ችግር ህጻናትን ከመደበኛ ትምህርት አፈናቅሏል፥ በርካታ ቤተሰቦችን ደግሞ ውድ እቃዎቻቸውን በመሸጥ ለከፍተኛ እዳና ኢኮኖሚያዊ ጫና ዳርጓልም ነው ያለው ድርጅቱ።
ኢስዋቲኒ፣ ሌሶቶ፣ ማዳጋስካር፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ዛምቢያ እና ዚምባብዌ በድርቁ የተጎዱ ሃገራት መሆናቸው ተገልጿል።
ከዚህ ውስጥ ዚምባብዌ ግማሽ የሚሆኑት ዜጎቻ ለከፋ የምግብ እጥረት የተዳረጉ ሲሆን፥ በርካታ ዝሆኖችም በርሃብ ሞተዋል።
ምንጭ፦ አልጀዚራ