ኮቪድ 19ን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ በመተግበር የሚያደርሰውን ጉዳት መቀነስ እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በከፍተኛ ሁኔታ በመዛመት ላይ ያለውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከልና ህብረተሰቡን ከአደጋው ለመታደግ በጤና ሚኒስቴር የተዘጋጀውን መመሪያ ቁጥር 30 መተግበርና የተቀናጀ ስራን ማከናወን እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
በመመሪያው አተገባበርና በተቀናጀ ስራው አስፈላጊነት ላይ ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴር፡ ከፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ የስትሪንግ ኮሚቴ አባላት በተሳተፉበት የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለምፀሀይ ጳውሎስ ኮቪድ-19 የሚያደርሰው ጉዳት እየከፋ በመምጣቱ ለህግ ማስከበሩ በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል፡፡
የኮቪድ-19 መስፋፋትና የአደጋው መብዛት የብዙዎችን ህይወት ከመቅጠፉ ሌላ ሌሎች የጤና አገልግሎቶችን ፈልገው ወደ ጤና ተቋማት ለሚመጡ ሰዎች የመተንፈሻ መሳሪያ እገዛ ለመስጠት የማንችልበት ደረጃ ላይ እየደረስን ነው ያሉት ወ/ሮ አለምፀሃይ መመሪያ 30 ከወጣ የቆየ ቢሆንም በህብረተሰቡ መዘናጋት ምክንያት ችግሩ እየተባባሰ በመሄዱ የህግ አማራጮችን ተጠቅሞ ህብረተሰቡን ከወረርሽኙ መታደግ አማራጭ የለውም ብለዋል፡፡
ቅናጅትና ትብብር፣ የኮሚኒክሽን ስራን ማጠናከር፣ የቁጥጥር ስርዓቱን ጠበቅ ማድረግና የሥራውን ዘላቂነት ማረጋገጥ ለሚሉት ነጥቦች ትኩረት መስጠት የግድ ነው ብለዋል ወ/ሮ አለምፀሃይ፡፡
ተገቢውን ጥነቃቄ በማያደርጉ ተቋማትና የተቋማት ኃላፊዎች ላይ ትኩረት አድርገን እንሰራለን ያሉት በፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ገለታ ስዩም በበኩላቸው ሥራው ላይ ምን ለውጥ እንዲመጣ በየጊዜው እየተገናኙ መምከርና ተገቢውን ሪፖርት በወቅቱ ማድረስ የግድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው የተጀመሩ መልካም ተግባራት ቢኖሩም ከችግሩ አንፃር ገና ባዙ መስራት ይጠይቀናልና ስራው የጋራ ርብርብን የሚጠይቅ መሆኑን በመረዳት ባለድርሻ አካላት የየራሳቸውን ተግባር በመከወን የፖሊስና የዓቃቤ ህግ ጫናዎችን ማቃለል አለባቸው ብለዋል፡፡
በተለይ ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ በማተኮርና በቀጣይ የሚከናወኑ የበዓላት ዝግጅቶችን ምክንያት በማድረግ እንዲሁም የተለያዩ የማቆያ ቦታዎችን በማዘጋጀት መመሪያውን በማይተገብሩት ላይ የማስተማርና ህግ የማስከበሩን ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ኮሚሽነር ጌቱ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ማስክ ባለማድረግ ከ70 ሺህ 000 በላይ ሰዎችን በመቆጣጠር የማስተማሪያ እርምጃ መወሰዱን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን