የዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ምክር ቤት ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በተገኙበት የዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ምክር ቤት ተመሰረተ፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ የምክር ቤቱ መቋቋም በገጽታ ግንባታ፣ የሃሰት መረጃ ስርጭትን ለማክሸፍ እና ሌሎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስከበር በተደራጃ መልኩ ለመስራት ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሜሪካ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለኮቪድ 19 መከላከል፣ ለህዳሴ ግድብ፣ በገጽታ ግንባታ እና አገራችን ላይ እየተደረጉ ያሉ ያልተገቡ ጫናዎችን በመቃወም እያደረጉት ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።
ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው በአሜሪካ የሚገኙ ወገኖች እያደረጉት ላለው ሁሉን አቅፍ ድጋፍ አመስግነው አጄንሲው ለሚቀርቡለት ጥያቄዎችን አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
አምባሳደር ፍጹም አረጋ በበኩላቸው ኤምባሲው ከዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ምክር ቤት አባላት ጋር በትብብር መስራቱን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በሌሎች ግዛቶች የሚገኙ የዳያስፖራ ወገኖችም ይህን አርዓያ በመከተል እያከናወኑ ያሉትን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎች በተደራጀ መልኩ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።
የዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ምክር ቤት በዋሽንግተን ዲሲ፣ ቨርጂኒያ እና ሜሪላንድ ከሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት የተውጣጡ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የተመሰረተ መሆኑንም በአሜሪካ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በምስረታው ወቅትም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚውል የ54 ሺህ ዶላር የተከፈለ ድጋፍ የተገኘ ሲሆን የመሃል ሜዳ ሚዲያ ባልደረቦች ደግሞ 50 ሺህ ዶላር አሰባስበው ለማስገባት ቃል መግባታቸውም ተገልጿል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን