የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ጥር ወር ላይ እንደሚካሄድ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ጥር ወር ላይ እንደሚካሄድ አስተናጋጇ ካሜሮን ገለፀች።
ትናንት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) እና የካሜሮን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያካሄዱትን ስብሰባ ተከትሎ የካፍ ፕሬዚዳንት የአፍሪካ ዋንጫ ከፈረንጆፐቹ ጥር 1 እስከ 29 ድረስ እንደሚካሄድ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ይዘጋጅ የነበረው በወርሃ ሰኔ እና ሐምሌ ላይ የነበረ ቢሆንም፥ እነዚህ ወራት በካሜሩን ዝናባማ ስለሚሆኑ ወደ ጥር እንዲዘዋወር ተደርጓል ተብሏል።
የጊዜ ለውጡ የተደረገው ካሜሮን ባቀረበችው ጥያቄ መሠረት መሆኑም ተነግሯል።
የካፍ ምክትል ዋና ፀሃፊ ቶኒ ባፉዬ በበኩላቸው በቀኑ ለውጥ ላይ ከካሜሮን ሜቲዮሮሎጂ ባለሥልጣናት፣ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ጋር እንዲሁም የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ ጋር ተወያይተናል ብለዋል።
ካሜሮን በ2019 የአፍሪካ ዋንጫን እንድታስተናግድ እድል ቢሰጣትም የማስተናገድ እድሉ በዝግጅት ሂደት መዘግየት ምክንያት ለግብፅ መሰጠቱ ይታወሳል።
ምንጭ፡-ቢቢሲ