ፍርድ ቤቱ ይገባኝ ሰሚ ችሎት በእነጃዋር እና በእነ እስክንድር ይግባኝ ክርክር በፕላዝማ መበላሸት ምክንያት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይገባኝ ሰሚ ችሎት በእነጃዋር መሐመድ እና በእነ እስክንድር ነጋ ይግባኝ ክርክር ላይ በፕላዝማ መበላሸት ምክንያት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ፡፡
ፍርድ ቤቱ በእነ ጃዋር መሐመድ ላይ የምስክር የመስማት ሂደት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የጸረ ሽብር እና የህገ መንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ባሰላፍነው ሳምንት የምስክር የመስማት ሂደቱ በግልጽ ችሎት እንዲሆን የሰጠው ብይን ተከትሎ አቃቤ ህግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለቱ ዛሬ ተሰይሞ የነበረ ቢሆንም ፕላዝማው ባለመስራቱ ምክንያት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በተመሳሳይ በእነ እስክንድር ነጋ የምስክር የመስማት ሂደት ላይ በይግባኙ ክርክር ለማድረግ የተሰየመ ቢሆንም በተመሳሳይ ለሁለቱም ለሚያዝያ 15 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ሆኖም በሁለቱም መዝገቦች በኩል ተከሳሾቹ የሚያነሱት መከራከሪያ ነጥብ ስላለ በአካል ተገኝተው ጉዳያቸው ይታይ ሲሉ ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ክርክር ማድረግ የሚቻለው ባሉበት ማረሚያ ቤት ሆነው በፕላዝማ ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል እነ ስብሓት ነጋ ያቀረቡት በዝግ ችሎት ምስክር ሊሰማብን አይገባም የሚል ይግባኝ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኘ ሰሚ ችሎት ክርክር ተደርጎበታል፡፡
በዚህ መሰረትም አቃቤ ህግ ቀርቦ በምስክር ጥበቃ አዋጅ 699/2003 መሰረት ጥበቃ እንደተደረገላቸው ለምስክሮቹ ደህንነት ሲባልም በዝግ ችሎት መደረጉ ተገቢ ነው ሲል መከራከሪያ ነጥብ አንስቷል፡፡
የስብሃት ነጋ ጠበቆች በበኩላቸው በዝግ ችሎት መሆኑ ተገቢነት የሌለው ነው በሚል ተከራክረዋል፡፡
ግራ ቀኙን ያደመጠው ችሎቱ ብይን ለመስጠት ለሚያዝያ 12 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በታሪክ አዱኛ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን