Fana: At a Speed of Life!

የመተከል ዞን ግብረሃይል እስካሁን ውጤታማ ተግባራትን ቢያከናውንም አሁንም ቀሪ ስራዎች ይጠበቁበታል – አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በመተከል ዞን የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረሃይል እስካሁን ውጤታማ ተግባራትን ቢያከናውንም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ቀሪ ስራዎች እንደሚጠበቁበት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎችን ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራል የመንግስት የስራ ሃለፊዎችን ያካተተ ልኡክ በመተከል ዞን የኮማንድ ፖስቱን ክንውን ገምግሟል።

በቆይታቸው የኮማንድ ፖስቱን ስራዎች ከመገምገም በተጨማሪ ከተለያዩ አመራሮች፣ ከአገር ሽማግሌዎችና የዞኑ ነዋሪዎች ጋር ጠቃሚ ውይይቶች ማካሄዳቸውን አቶ ገዱ ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመው ግብረ ሃይል የዜጎችን ሞት፣ መፈናቀልና ንብረት ውድመት በማስቆም ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ ማስፈን ቀዳሚ ተልዕኮው መሆኑንም አንስተዋል።

ለዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና ንብረት ውድመት ምክንያት የሆነው የታጠቀ ሽፍታ ላይ ጠንካራ እርምጃ በመውሰድ ረገድ ግብረሃይሉ ጥሩ ስራ ማከናወኑንም አቶ ገዱ ገልጸዋል።

ከታቀደው ግብ አኳያ ግብረ ሃይሉ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኑን የገለጹት አቶ ገዱ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ቀሪ ስራዎች ይጠበቁበታል ብለዋል።

በሌላ በኩል በሰላማዊ አማራጭ ችግሩን ለመፍታት በሀገር ሽማግሌዎች ጥረት ታጣቂዎች ወደ ሰላም እንዲመጡ የተሰራው ስራም ትልቅ ግምት የሚሰጠው መሆኑን አንስተዋል።

የታጠቀውን ሃይል በድርድር ወደ ሰላም እንዲገባ በማግባባት ከ3 ሺህ 400 በላይ ታጣቂዎች እንደተመለሱም አስታውሰዋል።

ከዞን እስከ ቀበሌ ፈርሶ የነበረውን የመንግስት መዋቅር አዲስ አደረጃጅት መፈጠርና ህብረተሰቡ ራሱን በራሱ እንዲጠብቅ ሚሊሻ በማሰልጠን ጭምር የተከናወነው ስራም የኮማንድ ፖስቱ የጥረት ውጤት መሆኑን አቶ ገዱ ገልጸዋል።

ያም ሆኖ ታጣቂውን ሃይል ትጥቅ በማስፈታትና መልሶ በማቋቋም እንዲሁም የሰለጠውን ሚሊሻ መዋቅሩን በማጠናከርና ትጥቅ በማሟላት ውስንነቶች አሉ ብለዋል።

በመተከል ንጹሃን ነዋሪዎች በከፍተኛ ደረጃ የጉዳትና የመፈናቀል አደጋ ደርሶባቸዋል ያሉት አቶ ገዱ፣ የተመሰቃቀለውን አካባቢ ወደ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ማምጣት የግብረሃይሉ  ያደሩ ቀሪ ስራዎች ናቸው ብለዋል።

እንደ አጠቃላይ የመተከል ዞንን መከላከያ ሰራዊት ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ወደ ቀደመ ሰላምና መረጋጋት እንዲመለስ ያደረገው ጥረት ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው መሆኑንም አቶ ገዱ ተናግረዋል።

በዞኑ ወደ ሰላም የተመለሰውን ሃይል አሰልጥኖ በፍጥነት ወደ ሰላማዊ ኑሮው እንዲገባ የማቋቋም እንዲሁም ትጥቅ ባለመፍታት የሸፈተውን ሃይል የማደን ስራው በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የመተከል ሰላምና መረጋጋት በመከላከያ ሰራዊት ጥረት ብቻ እውን ስለማይሆን ህብረተሰቡ፣ የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

በዚህ ዙሪያ በተለይ የአማራ ክልል ከቤኑሻንጉል ጉሙዝ ክልልና ከኮማንድ ፖስቱ ጋር አብሮ መስራት ይገባዋልም ብለዋል።

አቶ ገዱ የጉሙዝም ሆነ የሌላው ማህበረሰብ የጋራ ጠላት የሆነው የታጠቀ ሽፍታ እንጂ የህዝቡ አብሮነትና የጋራ እሴት እንዳለ መሆኑን መገንዘብም ይገባል ስለማለታቸው ኢዜአ ዘግቧል።

 

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.