Fana: At a Speed of Life!

የሙለር ሪል ስቴት ባለቤት የችሎት ቀጠሮ የምስክር ማስረጃ በሚገለብጡ ባለሙያዎች እጥረት ምክንያት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 30 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ለብይን ተቀጥሮ የነበረው የሙለር ሪል ስቴት ባለቤት የአቶ ሙሉጌታ ተስፋ ኪሮስ የችሎት ቀጠሮ የምስክር ማስረጃ በሚገለብጡ ባለሙያዎች እጥረት ምክንያት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የሙለር ሪል ስቴት ባለቤት አቶ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ መሬት ያለአግባብ ወስደዋል የመሬት ወረራ አድርገዋል ተብለው በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል በባለፈው ቀጠሮ የተሰማውን የዐቃቤ ህግ ምስክር ማስረጃ መርምሮ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ይዞ ነበር፡፡

ሆኖም በዛሬው ቀጠሮ ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ህግ ያሰማው ምስክር ማስረጃን የሚገለብጡ ከ30 የሪከርድ ባለሙያዎች ውስጥ በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ያሉት ሁለት ባለሙያ ብቻ መሆናቸውን በማብራራት በባለሙያ እጥረት ምክንያት ማስረጃው ተገልብጦ ከመዝገቡ ጋር አለመያያዙን ገልጿል።

በዚህ ምክንያት ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ህግ ያሰማውን የምስክር ማስረጃ መርምሮ ብይን ለመስጠት በድጋሚ ለሚያዚያ 19 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ተከሳሹ አቶ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ በጤንነቴ ምክንያት ከቤተሰብ ምግብ እንዲገባልኝ የታዘዘው ትዕዛዝ ተፈጻሚ አልሆነም በማለት ቅሬታ አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም “በማረሚያ ቤቱ በዞን 6 ከውጭ ሀገር እስረኞች ጋር እንድሆን ታዟል ነገር ግን ለደህንነቴ ስለሚያሰጋኝ ባለሁበት ዞን 4 ልቆይ” ሲሉ አመልክተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም ዳኛ ሲሟላ ትዕዛዝ እሰጥበታለሁ ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.