ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸውና ከ55 ዓመት በላይ ሆነው ተጓዳኝ የጤና ችግር ላለባቸው ግለሰቦች የኮቪድ 19 ክትባት ከሰኞ ጀምሮ ይሰጣል- የጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 23 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች እና ከ55 እስከ 64 ዓመት ሆነው የሚታወቅ ተጓዳኝ የጤና ችግር ያባቸው የህረተሰብ ክፍሎች ከመጪው ሰኞ ጀምሮ የኮቪድ 19 ክትባት አገልግት እንደሚሰጣቸው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ሚኒስትሯ ከ65 ዓመት በላይ የሆኑት የቀበሌ መታወቂያ በመያዝ እንዲሁም ተጓዳኝ የጤና እክል ያለባቸው ዕድሜያቸው ከ55 እስከ 64 የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ደግሞ ክትትል ከሚያደርጉበት ጤና ተቋም የሚከታተሉበትን የህክምና ማስረጃ በመያዝ አቅራቢያቸው በሚገኝ ጤና ጣቢያ ወይም የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በመሄድ እንዲመዘገቡና ክትባቱን መውሰድ እንዲጀምሩ ጥሪ አቅርበዋል::
ክትባቱ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ብሎም በወረርሽኙ ሊከሰት የሚችለውን ሞት እና ጽኑ ህመምን ለመቀነስ ያግዛል ብለዋል፡፡
የመከላከያ ዘዴዎችን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም፣ ርቀትን መጠበቅ እና የእጅ ንጽህናን መጠበቅ በየዕለቱ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ በአጽንዖት መናገራቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የጤና ሚኒስቴርም ክትባቱ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ደረጃ በደረጃ ለመስጠት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅ ወደ ተግባራዊ እርምጃ መግባቱ አስታውሷል፡፡
በኢትዮጵያ ለጤና ባለሙያዎች ከመጋቢት 4 ጀምሮ መሰጠት መጀመሩ ይታወሳል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!