የህዳሴው ግድብ ውሃ የሚተኛበት ስፍራ የደን ምንጣሮ ለማከናወን የሳይት ርክክብ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2013 (ኤፍቢሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ ውሃ የሚተኛበት ስፍራ ሁለተኛ ዙር የደን ምንጣሮ ለማከናወን ዛሬ በአሶሳ ከተማ የሳይት ርክክብ ተካሄደ፡፡
ርክክቡን ያካሄዱት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቴክኒክ ሙያ ስራ ዕድል ፈጠራ ኤጀንሲ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የኢንቫይሮመንታል እና ሶሻል ፕላኒንግ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ተስፋዬ በርክክቡ ወቅቱ እንዳሉት፤ ሁለተኛው ዙር የህዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት በመጪው ክረምት ይካሄዳል፡፡
ውሃው የሚተኛበት ቦታ ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍን ሲሆን ከዚህ ውስጥ በሁለተኛው ዙር በስፍራው በአራት ሺህ 854 ሄክታር ላይ የሚገኝ ደን ይመነጠራል ብለዋል፡፡
ስራው በጂ.ፒ.ኤስ. በታገዘ ካርታ እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡
ስራው ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር አመልክተው የአካባቢውን አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁመን ስራውን በወቅቱ እናጠናቅቃለን ነው ያሉት፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቴክኒክ ሙያ እና ስራ ዕድል ፈጠራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በሽር አብዱራሂም በበኩላቸው ስራውን ለማከናወን አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
ስራውን የሚያከናውኑ ከክልሉ ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ ስራ አጥ ወጣቶች በኢንተርፕራይዝ እንዲደራጁ ተደርጓል ብለዋል፡፡
“የህዳሴው ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደ አይን ብሌኑ የሚጠብቀው ነው” ያሉት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የኢኮኖሚ ዘርፍ አማካሪ አቶ ተፈሪ አበበ ናቸው፡፡
የክልሉ መንግስት ለግድቡ የሚያደርገውን ድጋፍ የደን ምንጣሮው ስራው እስኪጠናቀቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
ለደን ምንጣሮ ስራው ከ81 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡንና ከአምስት ሺህ በላይ የስራ እድል እንደሚፈጥር ተመልክቷል፡፡
የመጀመሪያ ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት ከመካሄዱ አስቀድሞ በስፍራው የሚገኝ ከአንድ ሺህ ሄክታር በላይ ደን ምንጣሮ ስራ መከናወኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!