የማምረቻ ተቋማት የሚያጋጥማቸውን የሃይል አቅርቦት ችግር መፍታት ያስችላል የተባለ ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የማምረቻ ተቋማት የሚያጋጥማቸውን የሃይል አቅርቦት ችግር መፍታት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአግሮ- ፕሮሰሲንግና ፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ተካ ገ/የሱስ ካሁን ቀደም የሃይል አቅርቦት እጥረትና መቆራረጥ በአምራች ኢንዱስትሪ ተቋማት ከሚነሱ ችግሮች ዋነኛው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ችግሮቹ አብዛኛዎቹ የማምረቻ ተቋማት በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ ተግዳሮት መሆኑን ገልጸው ስምምነቱ የዘርፉን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ትልቅ አማራጭ ነው ብለዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱ የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት ሁለቱ ተቋማት በቅንጅት እንዲሰሩ የሚያስችል እንደሚሆን ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው ስምምነቱ ሃገሪቱ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር የምታደርገውን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማሳለጥ ላቅ ያለ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
ተቋሙም የማምረቻ ተቋማት በሃይል አቅርቦት ዙሪያ የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመፍታት በቀጣይ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን