መንግስት እንዳይፀና በየጊዜው አላስፈላጊ ጫና የሚያደርጉ አካላትን በትብብር መመከት እንደሚገባ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት እንዳይፀና በየጊዜው አላስፈላጊ ጫና የሚያደርጉ አካላትን በትብብር መመከት እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምህንድስና መምህር እና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው እና በለንደን የግጭት አፈታት ጉዳይ ተመራማሪ ዶክተር ልዑል ሰገድ አበበ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ አሁን ላይ ከመቼውም ጊዜ በላይ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ያሰፈሰፉ አካላት እየተበራከቱበት ነው ብለዋል።
ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ከህዳሴው ግድብ እና በሌሎች የህግ ማስከበር ዘመቻ ዙሪያ አሁን ላይ ሊመጣ ያሰበውን አደጋ ለመጋፈጥ መዘጋጀት ይገባል ባይ ናቸው፡፡
አያይዘውም የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ተምሳሌቱ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለመላው የዓለማችን ድሃ ሀገራት መሆኑንም አውስተዋል፡፡
ፕሮፌሰር ዳንኤል ሁሉም ኢትዮጵያውያን በግድቡ ዙሪያ ከግብፅ በስተጀርባ ሌሎች አካላትም እንዳሉ ሊገነዘቡ እንደሚገባ ገልፀው፥ ከዚህ አኳያም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች፣ ምሁራንና ህብረተሰቡ በጋራ ለመመከት መዘጋጀት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በለንደን የግጭት አፈታት ጥናት ተመራማሪ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዶክተር ልዑልሰገድ አበበ በበኩላቸው ወቅታዊው የዲፕሎማሲ ስጋቶች የትውልደ ኢትዮጵያውያን ዜጋ ተኮር ዲፕሎማትነት አካሄድ እየቀየረው መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከቅርብ ወራት ወዲህም ዳያስፖራው እና ኤምባሲዎች ተቀራርበው መስራታቸውን በመልካም ጅማሮነት አንስተው አሁን የኢትዮጵያን እውነተኛ ገፅታ ለማስረዳት እየተሞከረ ስለመሆኑም አውስተዋል።
ዶክተር ልዑልሰገድ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያስረዳ በምሁራን አማካኝነት ለተመድ እና አውሮፓ ህብረት ፓርላማ ደብዳቤ መፃፋቸውን አስታውሰው፥ በመንግስት እና በትውልደ ኢትዮጵያውያን መካከል ያለው ትብብር ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት ገልፀዋል።
በሌላ በኩልም ሃገራዊውን ምርጫ እንደ መልካም እድል በመውሰድ የዲፕሎማሲ ስራ እየተሰራበት ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
ምሁራኑ አሁን ላይ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ ለመጣል እያሰፈሰፉ ያሉ ሃይሎችን በአንድነት መታገል እንደሚገባ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡
በስላባት ማናዬ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!