የሲሚንቶና የብረት እጥረት በግንባታ ሥራዎች ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲሚንቶና የብረት እጥረት በግንባታ ሥራዎች ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ገለጸ።
ሥራ ተቋራጮች ሰራተኞቻቸውን የመበተን ስጋት ውስጥ መግባታቸውንም ነው ያስታወቁት።
ማህበሩ በግንባታ ኢንዱስትሪ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ሥራ ተቋራጮች ለሰራተኞቻቸው ደመወዝ ለመክፈል መቸገራቸውን ገልጸዋል።
የማህበሩ ቦርድ ምክትል ሊቀመንበር ኢንጂነር የሱፍ መሐመድ እንደጠቀሱት፤ እየተባባሰ በመጣው የግንባታ አቅርቦት እጥረት የተነሳ ዘርፉ ችግር ላይ ወድቋል።
በተለይም ለግንባታ ወሳኝ የሆኑ የሲሚንቶና ብረት አቅርቦት እጥረት ጎልቶ እንደሚታይ ነው ያስረዱት።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ባንኮች ለተቋራጮች ቅድሚያ ክፍያ እንዳይፈጽሙ የጣለው እገዳ አሉታዊ ጫና ማሳደሩንም ተናግረዋል።
“ተቋራጮች ውሉ ላይ በ290 ብር ሲሚንቶ ቢሞላም፤ እስከ 700 ብር ሲሚንቶ ገዝቶ ሥራው እንዳይቋረጥ እየሰራ ሲሆን ከዚህ በላይ ምን ማድረግ ነበረበት” ሲሉም ጠይቀዋል።
የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግርማ ኃብተማሪያም “ዘርፉ ከገጠመው የግብዓቶች እጥረት ሌላ ከባንኮች የሚወጣው ገንዘብ ላይ የተጣለው ገደብ ችግር ላይ ጥሎናል” ብለዋል።
ችግሩን ለማቃለል ሥራ ተቋራጮችና ግብዓት አምራቾች በቀጥታ የሚገናኙበት ሁኔታ እንዲመቻችም መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ ከ22 ሺህ በላይ ሥራ ተቋራጮች እንዳሉ ከማህበሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!