መቀመጫቸውን ናይሮቢ ያደረጉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን ሚዛናዊ መረጃ እንዲያቀርቡ ተጠየቁ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም መቀመጫቸውን ናይሮቢ ያደረጉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን ሚዛናዊ መረጃ እንዲያቀርቡ ጠየቁ፡፡
አምባሳደሩ የመገናኛ ብዙኀን የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የሚሰሩት ዘገባ በመሰረታዊነት ሚዛናዊ ሊሆን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
አምባሳደሩ ይህንን ያሉት ለኬንያ የመገናኛ ብዙሃን እና መቀመጫቸውን ናይሮቢ ላደረጉ የዓለም አቀፍ ሚድያዎች መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
በመግለጫቸውም የኢትዮጵያ መንግስት የመገናኛ ብዙሃን ወደ ትግራይ ክልል ገብተው እንዲዘግቡ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን አስታውሰው ኤምባሲውም ወደ ኢትዮጵያ ለዘገባ የሚያመሩትን ሊያስተናግዳቸው ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
በትግራይ የመልሶ ማቋቋም እና የሰብዓዊ ድጋፍ መስጠት እንዲቻል ለሰብዓዊ ድርጅቶች ያልተገደበ ተደራሽነት መረጋገጡንም በዚሁ ወቅት ያስረዱት፡፡
በክልሉ ተፈፀመ የሚባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም በገለልተኛ አካል እንዲመረመሩ መንግስት ፈቃደኛ እንደሆነም አስታውሰዋል፡፡
የሱዳን መንግስት የኢትዮጵያን ሉዓላዊና በአስተዳደሩ ስር የነበረ ግዛት የዓለም አቀፍ ህግን ጥሶ መያዙን አምባሳደሩ ጠቅሰው ሁኔታዎች ወደ ነበሩበት ተመልሰው የድንበር ማካለሉ ከዚህ ቀደም በነበሩ አሰራሮች እንዲቀጥል በኢትዮጵያ በኩል ፍላጎት አለ ብለዋል፡፡
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይን በተመለከተ ግብፅና ሱዳን ከውዥንብር ታቅበው ስምምነቱን ከአፍሪካ-መር የሶስትዮሽ ንግግር መፍትሄ ለማግኘት ቢጥሩ የተሻለ እንደሆነ ስለመናገራቸው በኬንያ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!