Fana: At a Speed of Life!

ዶክተር ሊያ ታደሰ የኦክሲጅን ማምረቻ ማሽን ተከላ እገዛ ላደረገው የቢልና ሜልንዳ ጌትስ ፋውንዴሽንን አመሰገኑ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስቴር ዶክተር ሊያ ታደሰ የኦክሲጅን ማምረቻ ማሽን ተከላ እገዛ ላደረገው የቢልና ሜልንዳ ጌትስ ፋውንዴሽንን አመሰገኑ፡፡

ዶክተር ሊያ  በተጨማሪም የግዢ ሂደቱን ያስተባበረውን ክሊንተን ሄልዝ አክሰስ ኢኒሼቲቭ እንዲሁም መሳሪያውን ያቀረበውን ሜድስታር ሄልዝንም አመስግነዋል፡፡

በማህበራዊ ገጻቸው ላይ እንዳስታወቁት የኮቪድ ወረርሽኝን ከመከላከል ጎን ለጎን በኮቪድ ለሚያዙ የህብረተሰብ ክፍሎች የህክምና አገልግሎት በተሟላ መልኩ የሚሰጡ የጤና ተቋማት የማደራጀት እና የማዘጋጀት ስራ በጤናው ዘርፍ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

ከተደረጉ ዝግጅቶች ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው በመንግስት እና በግል ተቋማት ደረጃ የሚመረተውን የኦክሲጅን መጠን ማሳደግ፣ ስርጭቱን ወቅታዊ እና ፍትሀዊ ማድረግ እንዲሁም በጤና ተቋማት ደረጃ አጠቃቀሙን ማሻሻል እንደሆነም ነው የጠቀሱት፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት እንደ ሀገር የነበረው የኦክሲጅን ማምረት አቅም በእጥፍ ማሳደግ መቻሉን የገለጹት ዶክተር ሊያ የማሰራጨት አቅምን ለማሳደግ ከስድስት ሺህ በላይ የኦክሲጅን ሲሊንደሮች ተገዝተው መሰራጨታቸውን ነው ያስረዱት፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበሽታው የሚያዙ እና ወደ ህክምና ተቋማት የሚገቡ ታካሚዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ በመምጣቱ የኦክሲጅን አቅርቦት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

ይህንንም ተጽዕኖ ለማቃለል በኢትዮጵያ ከሚገኙ የኮቪድ ህክምና ተቋማት ውስጥ ብዙ የታካሚዎች አልጋ ያለው የሚሊኒየም ኮቪድ ህክምና ማዕከል ብዙ ኦክሲጂን የሚጠቀም በመሆኑ እና ታካሚዎች በኦክሲጅን አቅርቦት ማነስ ችግር ላይ እንዳይወድቁ የራሱ የሆነ የኦክሲጅን ማምረቻ ማሽን ተከላ ትናንት መከናወኑንም ነው የገለጹት፡፡

የኮቪድ 19ን አሳሳቢነት አሁንም በመገንዘብ ህብረተሰቡ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ በመጠቀም፣ አላስፈላጊ መሰባሰቦችን በማስወገድ እና ሲንቀሳቀሱ ርቀትን በመጠበቅ የበሽታውን ስርጭት መግታት ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

 

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.