የአድዋ ድል ሁሉም ኢትዮጵያውያን የጻፉት የጋራ ታሪካቸው ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) “የአድዋ ድል ሁሉም ኢትዮጵያውያን የጻፉት የጋራ ታሪካቸው ነው” ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።
‘አድዋ የሕብረ ብሄራዊነት አንድነት ዓርማ’ በሚል መሪ ቃል 125ኛው የአድዋ ድል በዓል እየተከበረ ይገኛል።
የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ባዘጋጀው የበዓሉ አከባበር ስነ-ስርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች፣ አባት አርበኞችና ሌሎች አካላት ታድመዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ “የዓድዋ ድል ሁሉም ኢትዮጵያውያን የጻፉት የጋራ ታሪካቸው ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን አንዱ የአንዱ ጠባቂና እረኛ በመሆን ከቀደምት አባቶች የአንድነት የድል ታሪክ መማር እንዳለባቸውም አንስተዋል።
“ኢትዮጵያዊነት ስጦታ አይደለም” ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ዋጋ ተከፍሎበት፣ ተለፍቶበት፣ አጥንትና ደም ተከፍሎበት በመስዋዕትነት የተገነባ ማንነት እንደሆነም ተናግረዋል።
ትውልዱ በኢኮኖሚ የበለፀገች እና ሁሉም ብሄር ብሄረሰብ በእኩል የሚኖርባት ኢትዮጵያን በመገንባት የራሱን ዓድዋ መድገም እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል።
“በዓድዋ ድል ላይ አንዱን ባይተዋር፤ ሌላውን የሩቅ ተመልካች፤ ሌላኛውን የድሉ ባለቤት በማድረግ የተሰራው የታሪክ ሽሚያ ሊስተካከል ይገባዋል”ም ነው ያሉት።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው “ዓድዋ የትናንት ድላችን የአሸናፊነት ስንቃችን ነው” ብለዋል።
የዓድዋ ድል ለመላው ጥቁር ህዝቦች ኩራትና የነፃነት አርማ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዓድዋ የአንድነትና የትብብር መንፈስ መማር እንደሚገባ የገለጹት ሚኒስትሯ፤ “ኢትዮጵያውያንም ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት አንድነታቸውን ማጠናከር ይገባቸዋል” ብለዋል በንግግራቸው።
የዓድዋን የስኬት ታሪክ ማወቅ፣ መውረስና ለትውልድ ማሻገር እንደሚያስፈልግ በመጥቀስም የድሉን ስኬት ሃገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ መድገም ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!