Fana: At a Speed of Life!

ለጥምቀት የሚመጡ የውጪ ቱሪስቶች ሌሎች የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎችን እንዲጎበኙ ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)  ለጥምቀት ክብረ በዓል ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጪ ቱሪስቶች በሀገሪቱ የሚገኙ ሌሎች የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎችን እንዲጎበኙ ዝግጅት መደረጉን ቱሪዝም ኢትዮጵያ ገልጿል።

ጥምቀት በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡን ተከትሎ የዘንድሮውን በዓል ለመታደም በርካታ የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች እንደሚመጡም ተጠቅሷል።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ፍፁም ካሳሁን ለኢዜአ እንዳሉት የበዓሉ ታዳሚ የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች ቁጥር ሊጨምር ስለሚችል በቂ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

የጎብኝዎችን የደህንነት እና የአገልግሎት ሁኔታ ምቹ ለማድረግ ከሆቴሎች፣ ከአስጎብኝ ድርጅቶች፣ ከመዳረሻ አካባቢ መስተዳድሮች፣ ከፀጥታ አካላት እና ከማህብረሰቡ ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፉ የሚጠበቀውን ጥቅም እያገኘች አይደለም ያሉት ዳይሬክተሩ፤  በአደባባይ ክብረ በዓላት ለመታደም የሚመጡ የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች በኢትዮጵያ የሚኖራቸውን ቆይታ ለማራዘም ስልቶች መነደፋቸውን ነው የገለጹት።

ጎብኝዎችን የሚያዋክቡ ሁኔታዎች እንዳይኖሩ መንግሥት ከተለያዩ አካላት ጋር እየተነጋገረ መፍትሔ እየሰጠ ነው ያሉት አቶ ፍጹም፤ በተለይ ያለ አግባብ የአገልግሎት ዋጋ የሚጨምሩ የንግድ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ቁጥጥር በማድረግ እና የጎብኝዎችን ደህንነት የሚያስጠብቅ “የቱሪዝም ሴኪዩሪቲ” በማዋቀር ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።

ከቀናት በፊት በጎንደር የተጀመረው “ህይወት በአብያተ መንግሥት” የተሰኘው ፕሮጀክት   ሌላው የጎብኝዎችን ቆይታ ለማራዘም ከሚያግዙት አንዱ  በመሆኑ፤ ለጥምቀት በዓል ወደ ስፍራው የሚያቀኑ ጎብኝዎች ከዋዜማው ቀደም ብሎ የጎንደር የፋሲለደስ አብያተ  መንግሥት የነገሥታትን ቆይታና የወቅቶቹ አጠቃላይ  ክዋኔ ይቀርባል ነው ያሉት።

ተመሳሳይ መርሃ ግብር በቀጣይ በአባጂፋር፣ በአፄ ዮሐንስ አብያተ መንግሥት እና በሌሎችም አካባቢዎች እንደሚተገበር ጠቅሰዋል።

በየአካባቢው ሰላምን በማረጋገጥ ና ጎብኝዎች በነጻነት እንዲጎበኙ መንግሥት ህግን ለማስከበር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን በመግለጽ ለዚህም የቱሪዝም ዘርፍ የቀውስ መሻገሪያ ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ነው የገለጹት።

በሀሰን ቱር ኤንድ ትራቭል ድርጅት  አስጎብኝ ነጃት በየነ እንዳለችው ኢትዮጵያ ብዙ የሚጎበኙ ሀብቶች ቢኖሯትም ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ጥቅም እያገኘች አይደለም።

ለጥምቀት እና ለሌሎች ጉብኝት የሚመጡ እንግዶችን የቆይታ ጊዜ ምቹና ረጅም ለማድረግ ሀገርን የሚወክሉ  አስጎብኝዎች  የጉብኝት መዳረሻ ስፍራዎችን በአግባቡ ማስተዋወቅና ማስተናገድ እንዳለባቸውም ገልጻለች።

ማህበረሰቡ አካባቢውን ምቹ በማድረግ፣ ጎብኝዎችን በመንከባከብና በቂ  አገልግሎት ማቅረብ አለበት የሚትለው ነጃት፤ “ሰላም ሳይኖር ጎብኝን መጠበቅ አይቻልም፤ ስለዚህ መንግሥት በሰላም እና በመሰረተ ልማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በስፋት መስራት አለበት” ብላለች።

ያለ አግባብ ዋጋ የሚጨምሩና ጎብኝዎችን የሚያዋክቡ አሽከርካሪዎችና የንግድ ተቋማት መኖራቸውን የጠቀሰችው አስጎብኝዋ፥ ድርጊቱ መታረም አለበት ብላለች።

በኢትዮጵያ የጥምቀት በዓልን በርካታ የውጭ ጎብኝዎች እንደሚታደሙ የገለፀችው ነጃት፤ ዘንድሮ “ቁጥሩ ከፍ ያለ ጎብኝ” ስለሚጠበቅ ድርጅታቸው ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ማድረጉንም ተናግራለች።

ጥምቀትን ጎንደር ላይ ለማየት የሚሄዱ ቱሪስቶች በዙሪያው ያሉትን ላሊበላን፣ ባህርዳርን እና ሌሎች አካባቢዎችንም እንዲጎበኙ ጠቋሚ መረጃዎችን በድረ-ገፅና በተለያዩ ስልቶች እያስተዋወቁ መሆኑንም  በአብነት ገልጻለች።

የባለሃገሩ  አስጎብኝ  ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ አየለ፥ የጥምቀት ክብረ በዓል በዩኔስኮ በመመዘግቡ ከወትሮው በርከት ያሉ ጎብኝዎች ስለሚመጡ ተቋማቸው የቱሪዝም መስቦችን ለማስተዋወቅና ለማስጎብኘት ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

ከአስጎብኝ ድርጅቶችም ባሻገር በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ አምባሳደሮች፣ መንግሥትና በየደረጃው ያለው ማህብረሰብ ሀገሩን በማስተዋወቅና የኢትዮጵያን ገፅታ በማጉላት ቱሪዝምን ማጠናከር አለባቸው ነው ያሉት።

“ቱሪዝም የበጎ ገፅታ መገንቢያ መንገድ ነው” ያሉት አቶ ተሾመ፤ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት እና የኢትዮጵያን ክብር ከፍ ለማድረግ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።

ከቱሪዝም ዘርፉ የሚጠበቀው ጥቅም እንዲገኝ በሀገሪቱ አልፎ አልፎ የሚታዩ ግጭቶችን በመፍታት፣ መሠረተ ልማቶችን ምቹ በማድረግና በየመዳረሻው የማረፊያና የመዝናኛ ሥፍራዎችን  በመክፈት ጎብኝዎችን ማርካት እንደሚገባም መክረዋል።

 

ምንጭ፦ ኢዜአ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.