አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ ለተመሰረተባቸው ክስ መከላከያ አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ ዓቃቤ ህግ ለመሰረተባቸው ክስ የመከላከያ ማስረጃ በዛሬው ዕለት አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ህዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ በተከሰሱባቸው ክሶች ላይ የመከላከያ ማስረጃ ታህሳስ 30 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል።
ተከሳሾቹ የመከላከያ ማስረጃ ሰነድ እና አሉን ካሏቸው 11 የቃል ምስክሮች ውስጥ ሶስቱን አቅርበዋል።
የተከሳሽ ጠበቆች በአንደኛው ክስ ካቀረቧቸው አራት የቃል ምስክሮች አንዱ በማረሚያ ቤት እንደሚገኝ በመጥቀስ በሁለተኛው ክስ በፅሁፍ ያቀረቧቸው የቃል ምስክሮች ግን ሊቀርቡ አለመቻላቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
አቃቤ ህግ በበኩሉ ጠበቆች የቃልና የሰነድ የመከላከያ ማስረጃቸውን ለፍርድ ቤት ሲያስገቡ ለአቃቤ ህግ በተገቢው ጊዜ እንዳልሰጡ ጠቅሷል።
በመሆኑም የቃል ምስክሮች ከሰነዶች ተነስተው የምስክርነት ቃላቸውን ሊሠጡ ስለሚችሉ ሰነዶችን መርምሮ ለመከራከር ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ምስክሮች ከአዲስ አበባ የመጡ መሆናቸውን በመጥቀስ ለአላስፈላጊ ወጪ እንዳይዳረጉ የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሠጡ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
የግራ ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤትም ጠበቆች ታህሳስ 23 ቀን 2012 ዓ.ም የቃልና የሰነድ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤት ዳኞች ሲያቀርቡ ለዓቃቤ ህግም ማቅረብ እንደነበረባቸው አስታውቋል።
ስለሆነም የቃል ምስክሮች ከሰነዶች ተነስተው የምስክርነት ቃላቸውን ሊሠጡ እንደሚችሉ ግምት ውስጥ በማስገባት ለጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በናትናኤል ጥጋቡ