Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት 420 የህወሃት ከፍተኛ የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮች መረጃ በማሰባሰብ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2013 (ኤፍቢሲ) ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በጁንታው ፀረ ሰላም እንቅስቃሴ ውስጥ የተሳተፉ 420 የህወሃት ከፍተኛ የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮች እንዲሁም 682  በወንጀል ድርጊት  የተሳተፉ  የጁንታው አባላት ላይ መረጃ በማሰባሰብ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡

ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የተያዘውን በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወር የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ ያካሄደውን ግምገማ  አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ፤ ከትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻ ጋር በተያያዘ በጁንታው ፀረ ሰላም እንቅስቃሴ ውስጥ ሲሳተፉ  የቆዩ  420  የህወሃት ከፍተኛ  የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮች እንዲሁም 682  በወንጀል  ድርጊት  የተሳተፉ  የጁንታው አባላት በቁጥጥር ሥር ውለው በህግ ተጠያቂ  እንዲሆኑ አስፈላጊው  መረጃ ተዘጋጅቶና ተደራጅቶ ለጸጥታ አስከባሪ ዘርፉ መሰጠቱን  ገልጿል፡፡

አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በ2010 ዓ.ም ካካሄደው ሪፎርም በኋላ  የተቋሙ አባላት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በመሆን እንዲያገለግሉ አቅጣጫ አስቀምጦ  እስከታች  በማውረድ ተግባራዊ ቢያደርግም፤ የተቋሙን አሠራር በመጣስ  የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተልዕኮ  ለማስፈጸም  በተግባር  የተሳተፉ ሰራተኞች ላይ   እርምጃ መወሰዱን አመልክቷል።

በተለይ በተቋሙ የውጭ ስምሪት ሥራ ላይ የነበሩ 3 አባላት ከአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መርህ ውጪ ከጁንታው ቡድን  ጋር በማበር የዲፕሎማቲክ ሽፋናቸውን አላግባብ  በመጠቀማቸው  እንዲሁም 20 አባላት ደግሞ መረጃን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሲጠቀሙ በክትትል ስለተደረሰባሰቸው  በተቋሙ ህግና አሰራር  መሠረት  እርምጃ  እንዲወሰድባቸው መደረጉን  ገልጿል።

እንደ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ማብራሪያ፤ በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ለመንግስት አስፈላጊ የደህንነት መረጃ ሪፖርቶች ሲቀርቡ ነበር፡፡  የህግ ማስከበር ዘመቻው በድል እንዲጠናቀቅ በመደገፍ ጁንታው በትግራይ ክልል የሰሜን ዕዝ ላይ ከፈጸመው አሠቃቂ ጥቃት ጋር በተያያዘ የጁንታው ቁልፍ የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮችና ሰራዊታቸውን እንቅስቃሴ፤ የተለያዩ ወታደራዊ ሚስጥሮችን፣ ድብቅ ሴራዎችን፣ የጁንታውን ትልሞችና  የሽብር ሥራዎችን የሚያጋልጡ መረጃዎችንና ሰነዶችን በማሰባሰብ  ረገድ ተቋሙ ውጤታማ ሥራ ማከናወኑ በግምገማው ወቅት መገለፁን መረጃው አመልክቷል።

በሀገር ውስጥ  የሚንቀሳቀሱትን የኦነግ ሸኔና የጉምዝ ታጣቂዎችን እንዲሁም የድንበር ተሻጋሪ ወንጀለኞችን  እንቅስቃሴዎች ለመግታት  በሚደረገው ጥረትም በአጠቃላይ ከ432  በላይ ተጠርጣሪዎች  ላይ  መረጃ  በመሰብሰብ  ለሚመለከተው አካል  እንዲሰጥ  ማድረጉን ገልጿል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት በማወክ ፍላጎታቸውን ለማራመድ የሚንቀሳቀሱ አሸባሪ ሀይሎችና ቡድኖች በሀገሪቱ ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት ላይ ስጋት እንዳይደቅኑ ለማድረግ በተከናወነው የክትትል ሥራ 233 ተጠርጣሪዎች ላይ መረጃ  በመሰብሰብ ለሚመለከታቸው አካላት የተለካ ሲሆን፤ 13  ተጠርጣሪዎች ደግሞ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተመልክቷል።

በተቋሙ ፕሮፌሽናል፣ ትውልድ ተሻጋሪና በቴክኖሎጂ  የተደገፈ  ስራ እንዲከናወን  በተደረገው ሁሉን አቀፍ ሪፎርም   አመርቂ  ውጤት እየተመዘገበ ሲሆን፤ በተያዘው የበጀት ዓመትም  የአገልግሎት  መሥሪያ ቤቱን ተልዕኮና አላማ የሚወክል አዲስ  ሎጎ ሥራ ላይ  እንዲውል፤ በተቋሙ ምቹ የስራ አካባቢ ለመፍጠርና ለተልዕኮው ስኬት አስፈላጊ የሆኑ ግብዕቶችን ለማሟላት የተጀመሩ ስራዎች አበራታች መሆናቸውን በሚቀጥለው ግማሽ አመትም ይሄው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል  አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በላከው መረጃ  አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪም ተቋሙ፤ በሀገር ውስጥ ከህዝቡ የሚሰበሰቡ መረጃዎችን ጥቅም ላይ በማዋል፤ ከውጭ ከተለያዩ ሀገራት አቻ የመረጃ የደህንነት ተቋማት ያለውን ግንኙነት በማጠናከርና የመረጃ ልውውጥ በማድረግ መረጃ የመሰበሰብ አቅሙን ለማጎልበት እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች በጥሩ ጎን ተገምግመዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳል ከላይ በጥንካሬ የተገመገሙ ጉዳዮች ቢኖሩም፤ የተጀመረውን ሃገራዊ የለውጥ ሪፎርም በሃሰት ለማደናቀፍ፤በመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፤ በመንግስት የአሰራር  ስርዓቶች፤ ሲስተሞችና አጠቃላይ መዋቅሩ ላይ አልፎ አልፎም በፀጥታና ደህንነት ተቋማት ላይ የሃሰትና የበሬ ወለደ ስም የማጠልሸትና የማጥፋት እንቅስቃሴ መንግስት በህዝብ ላይ ያለውን ተቀባይነት ጥራጣሬ ውስጥ ለመክተትና የሃገርን ሰላም ለማደፍረስ ሌት ተቀን ከሚሰሩ የውስጥና የውጭ ሃይሎች አጀንዳ በመቀበል የሚሰሩ አካላት ላይ መረጃ በማሰባሰብ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ ክፍተት መኖሩ በግምገማው የታየና በቀጣይ ተቋሙ በዚሀ ጉዳይ ላይ በትኩረት መስራት እንዳለበት ከመግባባት ላይ መደረሱ ተጠቁሟል፡፡

መጪው ሀገራዊ ምርጫም ያለምንም የፀጥታና የደህንነት ስጋቶች በሰላም እንዲጠናቀቅ ተቋሙ ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ለመስራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን  አገልግሉት መስሪያ ቤቱ  በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.