የቻይና ተመራማሪዎች በከፍተኛ ሙቀት ወቅት የአውሮፕላኖችን ሁኔታ መከታተያ መንገድ ይፋ አደረጉ
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 29 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና ተመራማሪዎች እጅግ በጣም ከፍተኛ በሆነ የሙቀት ወቅት የአውሮፕላኖችን ሁኔታ መከታተል የሚያስችል ዘዴ ይፋ አደረጉ።
አዲሱ ቴክኖሎጂ አውሮፕላኖች ከ800 እስከ 1 ሺህ 300 ዲግሪ ሴሊሺየስ ባለው የሙቀት መጠን ውስጥ ሲሰሩ በአውሮፕላኖቹ ውስጥ የሚከሰተውን መዋቅራዊ ብልሽት መለየት የሚያስችል መሆኑን ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል።
ይህም እጅግ ከፍተኛ የሆነ ሙቀትና ቅዝቃዜ ባለበት የአየር ንብረት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አውሮፕላኖችን አጠቃላይ ሁኔታ ለመከታተል የሚያግዝ ነው ተብሏል።
ከዚህ ባለፈም አውሮፕላኑ በከፍተኛ ፍጥነት በሚበርበት ወቅት የሚያጋጥመውን ከፍተኛ ሙቀት ተቋቁሞ በረራውን መቀጠል ስለመቻል አለመቻሉም ለመወሰን እንደሚያግዝም ከተመራማሪዎቹ አንዱ የሆኑት ዋንግ ዚዮንግ ተናግረዋል።
የአውሮፕላኖች አሰራር እጅግ ከፍተኛ በሆነ የሙቀት መጠን ውስጥ የሚደረግን በረራ መቋቋም ስለመቻል አለመቻሉ በመወሰን አዲስ ለሚሰራ የአውሮፕላን ንድፍ እንደ ማጣቀሻ ሆኖ ያገለግላልም ነው የተባለው።
ከዚህ አንጻርም የአውሮፕላን አካላትን ንድፍ ለማሻሻል እንዲሁም ቀላል እና ብዙ ጭነቶችን መሸከም የሚችሉ አውሮፕላኖችን ለመስራት በሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችልም ተገልጿል።
ምንጭ፦ ሲ ጂ ቲ ኤን