ሳላህዲን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና ቡድን ተለይቶ ከተስፋ ቡድኑ ጋር ልምምድ እንዲሰራ ውሳኔ ተላለፈበት
አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ሳላህዲን ሰኢድ ከስነ ምግባር ግድፈቶች ጋር ተያይዞ ውሳኔ እስከሚተላፍበት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና ቡድን ተለይቶ ከተስፋ ቡድኑ ጋር ልምምድ እንዲሰራ የቅዱስ ጊዮርስ ስፖርት ማህበር ስራ አመራር ቦርድ ውሳኔ አስተላለፈ።
የቅዱስ ጊዮርስ ስፖርት ማህበር ስራ አመራር ቦርድ በ2013 ዓ.ም የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለሚሳተፈው ቡድን ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ በተሟላ ሁኔታ ውጤታማ እንዲሆን በሁሉም መስኮች አስፈላጊውን ሁሉ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ ክለቡ ከተደረገለትና ከሚጠበቅበት ውጤታማነት አንጻር አርኪ የሚባል እንቅስቃሴዎችን እያደረገ አይደለም ብሏል ቦርዱ፡፡
የስራ አመራር ቦርዱ በቅርቡ ባደረገው ስብሰባም በቡድኑ ውስጥ ያሉ ችግሮችን በተመለከተ ሰፊና ጥልቅ ውይይት አድርጎ፤ የተለያዩ የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ መመሪያዎችን መስጠቱን ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ቦርዱ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች የሆነው ሳላህዲን ሰኢድ በተደጋጋሚ ጊዜ የፈጸማቸውን የስነ ምግባር ግድፈቶች በማየት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ማድረጉ ተጠቁሟል፡፡
˝ሳላህዲንን ከዋናው ቡድን ጋር ለተጨማሪ ጊዜ አብሮ እንዲቆይ መፍቀድ በውድድሩ ላይ እየተፋለመ ለሚገኘው ቡድን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ከቡድን መሪው በሥነ ምግባር ዙሪያ በዝርዝር በሚቀርበው ሪፖርት ላይ በቦርዱ ውሳኔ እስከሚገኝ ድረስ ከተስፋ ቡድኑ ጋር ልምምዱን እያደረገ እንዲቆይ መመሪያ ተሰጥቷል˝ ሲል ነው ክለቡ የገለፀው፡፡
በቅርቡም የቡድኑ አልጣኝ ዳቪድስ ማሂር በቡድኑ ውስጥ ያሉ ችግሮችን በአፋጣኝ እንዲያስተካክሉ ከጅማ ወደ አዲስ አበባ በመጥራት በቦርዱ መመሪያ ሰጥቷቸዋል ነው የተባለው፡፡ ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!