Fana: At a Speed of Life!

በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ከ149 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር በ2013 በጀት አመት የመጀመሪያው ስድስት ወር 149 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን አስታወቀ።

የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው የተቋሙን የስድስት ወር አፈጻጸም አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በስድስት ወሩ146 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 149 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የእቅዱን 102 በመቶ ማሳካት መቻሉን አብራርተዋል።

ይህም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ21 ቢሊየን ብር ወይም በ17 በመቶ እድገት እንዳለውም ነው የጠቀሱት ።

ከዚህ ውስጥ ከሃገር ውስጥ ገቢ 88 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ማግኘት ታቅዶ 93 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር የተሰበሰበ ሲሆን፥ ከወጪ ንግድ ደግሞ 58 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ለማግኘት ታቅዶ 55 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ተገኝቷል ነው ያሉት ።

ከብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር 73 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ለማግኘት ታቅዶ 130 ሚሊየን ብር ሲገኝ ይህም የእቅዱን 176 በመቶ መሆኑ ተመላክቷል።

ሚኒስቴሩ በጥቅሉ ካገኘው ገቢ የተለያዩ ወጪዎችን ቀንሶ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ገቢ ለማድረግ ካቀደው 139 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር 130 ነጥብ 4 ቢሊየን ብሩን ገቢ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።

ይህም የእቅዱን 93 ነጥብ 45 በመቶ መሆኑን ጠቁመው ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ15 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ጭማሪ ማግኘት መቻሉን አንስተዋል።

የኮሮና ቫይረስ፣ በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ስራውን ተከትሎ በክልሉ የሚገኙት የተቋሙ ቅርንጫፎች ለሶስት ወራት ስራ አለመስራታቸው እንዲሁም በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች በገቢ አሰባሰቡ ላይ እንቅፋት መሆናቸው ተነስቷል።

በሃይማኖት ኢያሱ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.