Fana: At a Speed of Life!

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኮሮናን በመከላከል ምርት እንዳይስተጓጎል ያደረገው ጥረት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው – የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኮሮናን በመከላከል የምርት ሂደቱ እንዳይስተጓጎል እያደረገ ያለው ጥረት ለሌሎችም ተቋማት ምሳሌ እንደሚሆን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ።

የኮሚቴው አባላት በፓርኩ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን የቡድን መሪው አቶ ዘውዱ ከበደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ፈሶባቸው የተቋቋሙት የሥራ ዕድል ፈጠራን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን እንዲሁም የውጭ ምንዛሪን ለማሳደግ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህ ረገድ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከመንግስት የተሰጠውን ተልዕኮ እየተወጣ መሆኑን ባደረጉት ቅኝት ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይ ኮሮናን መከላከል መሠረት ባደረገ መልኩ በውስጡ ያሉ ኩባንያዎች ሳይዘጉ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ በማድረግ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው የከፋ ጫና ውስጥ እንዳይገባ ያደረገው ጥረት ውጠታማ መሆኑን አስረድተዋል።

በኩባንያዎች ውስጥ የተቀጠሩ ሠራተኞች የሚከፈላቸው ደመወዝ አነስተኛ እንደሆነ መረዳታቸው የገለጹት አቶ ዘውዱ በጊዜ ሂደት ማሻሻያዎች በማድረግ የሚስተካከል እንደሆነም ተናግረዋል።

አሁን ላይ የሠራተኛው ደመወዝ ከፍ በማድረግ መደገፍ ባይቻልም በተለይ የመኖሪያ ቤት ችግራቸውን ማቃለል እንደሚቻልና ኢንዱስትሪ ፓርኩም በዚህ ላይ ጠንክሮ መስራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍፁም ከተማ በበኩላቸው ፓርኩ ተቆጥሮ የተሰጠውን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በፓርኩ ውስጥ ከ28 ሺህ በላይ ሠራተኞች እንዳሉ ጠቁመው፤ ኩባንያዎች ውስጥ በሚሰሩበት ወቅት የተሟላ የቴክኖሎጂ እውቀት እንዲቀስሙ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነም ተናግረዋል።

ኢንዱስትሪ ፓርኩ ሀገራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

የሠራተኞችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለልም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያመለከቱት  አቶ ፍፁም፤ በአሁኑ ወቅት ኩባንያዎች ቦታ ተሰጥቷቸው ሠራተኞቻቸው ቤት እንዲገነቡ በሂደት ላይ እንደሚገኙ ማስረዳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የቤት መስሪያ ቦታ ያላቸው በፓርኩ አቅራቢያ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ከባንክ ብድር አግኝተው ለኪራይ የሚሆኑ ቤቶችን በመገንባት ችግሩን ለመቀነስ እየሰሩ መሆኑንም አብራርተዋል።

 

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.