የህዳሴ ግድብ ግንባታን በበጎ ጎን የማታየው ግብፅ ዓለም አቀፋዊ የሀይል ማዕከል ለመሆን እየጣረች ነው
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ሀብቷን በመጠቀም ሀይል ለማመንጨት የምታደርገውን ጥረት በተለያዩ መንገዶች ለማደናቀፍ በርካታ ጥረቶችን እያደረገች የምትገኘው ግብፅ ቀጠናዊ የሀይል ማዕከል ለመሆን እየጣርኩ ነው ብላለች።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ እየተገነባ የሚገኘው የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ 6 ሺህ ሜጋዋት ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል።
ግድቡ ለኢትዮጵያውያን የዘመናት የሀይል ጥያቄ ምላሽ እንደሚሰጥ የሚጠበቅ ቢሆንም የኢትዮጵያ እድገት እና ለውጥ በበጎ ጎኑ የማታየው ግብፅ የግንባታ ሂደቱን ለማደናቀፍ ስትሰራ ማየቱ የተለመደ ነው።
በዚህም የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ለግድቡ ግንባታ ከሀገራት እና ከተቋማት ብድር እንዳታገኝ እያደረገች ቆይታለች።
ሆኖም ይህ ጫና ያልበገራት ኢትዮጵያ ከመንግሥት በጀት እና በኢትዮጵያ ህዝቦች ድጋፍ ብርሃንን በተስፋ ለሚጠብቁት ኢትዮጵያውን ለመስጠት የህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተሰራ ይገኛል።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደትን ለማደናቀፍ ከኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲው ላይም ጫና ለመፍጠር እየጣረች የምትገኘው ግብፅ ራሷን ቀጠናዊ የሀይል ማዕከል ለማድረግ እየሰራች መሆኑን አህራም አስነብቧል።
አህመድ ኮብ የተባሉ ግለሰብ በአህራም ኦንላይን ላይ ባስነበቡት ፅሁፍ ግብፅ ተፈጥሯዊ ጋዝ እና በታዳሽ ሀይል የነበሩባትን ክፍተቶች በመሙላት የሀይል ማዕከል እየሆነች ትገኛለች ሲሉ ይናገራሉ።
በተለይ ከተፈጥሮ ጋዝ ተያይዞ የነበውን ችግር በመቅረፉ እና አዲስ የተፈጥሮ ጋዝ ክምች በመገኙት ግብፅ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ለመላክ ዝግጁ ሆናለች በማለት አስፍረዋል።
በዚህ በተገኘው ክምችት ግብፅ በየቀኑ 6 ነጥብ 8 ቢሊየን ኪዮቢክ የተፈጥሮ ጋዝ በማምረት ለሌሎችም ለመትረፍ መንገድ ላይ ናት ብለዋል።
በአሌክትሪክ ሴክተሩ በዳባ የኒውክሌር ሀይል ማመንጫ ጨምሮ በታዳሽ የሀይል እና በሌሎች አዲስ የሀይል ማንመንጫዎች በምታመነጨው የተትረፈረፈ ሀይል ግብፅ የኤሌክትሪክ ላኪ ሀገር እንደሚያደርጋት ይናገራሉ።
እኒህን ግብፃዊ ምሁር ጨምሮ ሌሎች የሀገሪቱ ምሁራን በጨለማ ውስጥ ለሚገኙ 55 በመቶ ዜጎቿ የኤሌክትሪክ ሀይል ለማቅረብ ለምታትረው ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ለመጠቀም መጣሯን እንደ ሀጢአት ሲወስዱት እየታየ ነው።
በግብፅ ያለው የኤሌክትሪክ ሀይል ስርጭት ዓመታዊ የኢንቨስትመንት ፍሰት 700 ሚሊየን 262 ሺህ ዶላር ደርሷል።
ከነፋስ ፣ ፀሀይ እና በሌሎች መንገዶች የምታመነጨው የኤሌክትሪክ ሀይል ፍላጎቷን ያሟላላት ግብፅ በፈረንጆቹ 2020 የአሌክትሪክ ሀይል የማመንጨት አቅም 54 ሺህ ሜጋዋት ደርሷል።
አሁን ላይ ለሱዳን ፣ ጆርዳን እና ሊቢያ የአሌክትሪክ ሀይል የምታቀርበው ሀገሪቱ በቀጣይ ዓመታትም ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ግሪክ እና ሳይፕረስ ጋር የአሌክትሪክ አቅርቦት ግንኙነት ለመፍጠር እየሰራች ነው።
በዚህም 15 ሺህ ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ሀይል በማቅረብ የአፍሪካ፣ የዓረብ እና የአውሮፓ ሀገራትን በማገናኘት ከቀጠናዊ ባሻገር ቀዳሚ ዓለም አቀፍ የአሌክትሪክ ሀይል ማዕከል ለመሆን አቅዳለች።
በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋን እና ተደራሽነቱ 44 ከመቶ አካባቢ እንደሚሆን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይህም ከግማሽ በላይ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት እንዳይኖራቸው ያደረገ ሲሆን ግብፃውያን ግን ይህ የኢትዮጵያውያን ችግር የሚታያቸው አይመስልም።
በኤፍሬም ምትኩ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!