Fana: At a Speed of Life!

የኮቪድ 19 የጽኑ የህሙማን ቁጥር በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ ከጤና ተቋማት የመቀበል አቅም በላይ እየሆነ መጥቷል- ዶ/ር ሊያ ተደሰ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮቪድ 19 የጽኑ የህሙማን ቁጥር በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ ከጤና ተቋማት የመቀበል አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን ጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።

ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ዳግም ትኩረት እንደሚያስፈልግም ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ በአጽንኦት ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት የጽኑ ሕክምና አገልገሎት የሚፈልጉ የህሙማን ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሆኑን የገለፁት ዶክተር ሊያ፥ በተለይ በአዲስ አበባ ከጤና ተቋማት የመቀበል አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱንም ተናግረዋል።

በየቀኑ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ለሕክምና ክትትል ወደ ሕክምና ማዕከል ከሚገቡት ታማሚዎች ውስጥ በአማካይ 305 የሚሆኑት ጽኑ ህሙማን ሕክምና ክፍል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፥ ከነዚህ ውስጥም ከ40 እስከ 45 የሚሆኑት ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሣሪያ የሚጠቀሙ ናቸው ብለዋል።

እስካሁን ባለው ሁኔታ የጽኑ ሕክምና ክፍል ከገቡት ውስጥ 59 በመቶ ያህሉ ህይውታቸው እንዳለፈም በቀረበው ገለጻ ላይ ተብራርቷል።

በሕብረተሰቡ ውስጥ እየተስተዋለ ያለው ከፍተኛ ቸልተኝነትና መዘናጋት፤ በሽታው ጠፍቷል ወይም በሽታው በኔና በቤተሰቤ ብሎም በማሕበረሰቤ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ብሎ ካለመረዳትና እና እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የሚጠበቅበትና ሚና አለመወጣቱ  አሁን ላይ ለሚስተዋለው ችግር እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሱ ስለመሆናቸውም ተገልጻል።

ይህ ሁኔታም በዚህ ከቀጠለ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ እንደ ሀገር ካለው ውስን የጽኑ ህሙማን እንክብካቤ አቅም በላይ ሊሆን እንደሚችልም ጭምር የጤና ሚኒስተር ደክተር ሊያ ታደሰ ከፍተኛ ስጋታቸውን አስታውቀዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እያደረሰ ያለው እና ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖዎችን የመከላከል ስራ ለአፍታም ቢሆን ጊዜ የማይሰጠው እና ለተወሰኑ ተቋማት የማይተው በመሆኑ እንያንዳንዱ ሰው በእያንዳንዷ ደቂቃ የምናከናውነው ቅድመ ጥንቃቄ በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ እና አራዓያነት ሊሆን እንደሚገባ ዶክተር ሊያ ታደሰ መልዕክታቸውን በአጽንኦት አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 የላብራቶሪ ምርመራ አቅም በየጊዜው በማሳደግ እስከአሁን ለ1 ሚሊየን 683 ሺህ 558 ሰዎች የኮቪድ-19 የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸዋል።

ከእነዚህም ውስጥ 114 ሺህ 834 ማለትም አጠቃላይ ከተመረመሩት 6 ነጥብ 8 በመቶ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ  እንደተገኘባቸው ተረጋግጧል።

ከነዚህ ውስጥም የ1 ሺህ 769 ማለትም ቫይረሱ በምርመራ እንደተገኘባቸው ከተረጋገጠ ሰዎች 1 ነጥብ 5 በመቶው በበሽታው ሕይወታቸው ማለፉን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.