Fana: At a Speed of Life!

የሕወሃት ጁንታ በፈጸመው ጥቃት የኤሌክትሪክ ሃይል የተቋረጠባቸው ከተሞች እስከ ሳምንቱ መጨረሻ መብራት ያገኛሉ ተባለ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 30 ፤2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕወሃት ጁንታ በፈጸመው ጥቃት የኤሌክትሪክ ሃይል የተቋረጠባቸው ከተሞች እስከ ሳምነቱ መጨረሻ መብራት እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታወቀ።
ቡድኑ በኅይል ማስተላለፊያ መሰረተ ልማት ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ለአንድ ወር ያክል የኤሌክትሪክ ሃይል ተቋርጦባቸው የነበሩ የትግራይ ክልል ከተሞች ጥገናው ተጠናቆ በሳምንቱ መጨረሻ ድረስ ሙሉ በሙሉ የሃይል ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።
በትግራይ ክልል በርካታ አካባቢዎች ከተከዜ ሃይል ማመንጫና ከአሸጎዳ የንፋስ ሃይል ማመንጫዎች የመብራት አገልገሎት እንደሚያገኙ ይታወቃል።
ከብሔራዊ የሃይል ቋት ከኮምቦልቻና ባህር ዳር ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ 230 ኪሎ ቮልት ተሸካሚ መስመሮችም ሃይል ያገኛሉ።
ይሁን እንጂ የህወሃት ፅንፈኛ ቡድን በእነዚህ የሃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና በሃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ገልጿል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ፤ የ230 ኪሎ ቮልት ሃይል ተሸካሚ መስመሮች ከአላማጣ-መሆኒ፣ ከአላማጣ-አሸጎዳ እንዲሁም ከአሸጎዳ-መቀሌ የሃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲሉ ለኢዜአ ተናግረዋል።
“የ66 ኪሎ ቮልት ተሸካሚ የአላማጣ-ማይጨው፣ አላማጣ-ሰቆጣ ሃይል ማስተላለፊያ መስመሮች የሽቦና ኢንሱሌተር እንዲሁም በማከፋፊያ ጣቢያዎች ላይም ጉዳት አድርሷል” ብለዋል።
በዚህ የተነሳ መብራት ተቋርጦ እንደነበር ገልጸው፤ ድርጅቱ ልዩ የጥገና ኮሚቴ በማዋቀር የጉዳት መጠኑን በመለየት ግብዓትና የሰው ሃይል አሟልቶ የጥገና ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።
በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ከባህር ዳር በመተማ፣ ወልቃይት፣ ሽሬና አድዋ መስመር እንዲሁም በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ ማዕከሉን ደሴ በማድረግ አላማጣ፣ መሆኒ፣ መቀሌ፣ አክሱምና ውቅሮን የሚሸፍን የጥገና ቡድን ወደ ስራ መሰማራቱን ገልጸዋል።
“እስካሁንም የሁመራ፣ አላማጣና መሆኒ ማከፋፈያ ጣቢያዎች በመጠገን በአካባቢው ከተሞች ሙሉ በሙሉ የሃይል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል” ብለዋል።
መቀሌን ጨምሮ ሌሎች ማከፋፊያ ጣቢያዎችና ማስተላለፊያ መስመሮችም ጥገና እየተከናወነላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የጥገና ስራው በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ሁሉንም የትግራይ ክልል ከተሞችን የሃይል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ሞገስ ተናግረው፤
“እስከ መጪው እሁድ ድረስ በሁሉም አካባቢዎች ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክ ሃይል ችግር ይፈታል” ብለዋል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል
https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.