መርማሪ ፖሊስ ለሽብር ወንጀል ከ250 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ መሰብሰባቸውን በማስረጃ አረጋግጫለው ባላቸው አራት ተጠርጣሪዎች በ3 ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ በፍርድቤት ታዘዘ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 30፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መርማሪ ፖሊስ ለሽብር ወንጀል ማስፈጸሚያ ከ250 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ መሰብሰቡን በማስረጃ አርጋግጫለው ባለው በተስፋሁነኝ ንጉስ ጨምሮ አራት ተጠርጣሪዎች በ3 ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ በፍርድቤት ታዘዘ።
ተጠርጣሪዎቹ በሶስት ሺህ ብር ዋስ አስይዘው እንዲወጡ የፈቀደው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድቤት 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው ።
በመዝገቡ ተካተው የነበሩ አጠቃላይ ተጠርጣሪዎች ስድስት የነበሩ ሲሆን ÷መርማሪ ፖሊስ ማስረጃ ስላላገኘባቸው 3ኛ እና 6ኛ ተጠርጣሪዎችን በዋስ መልቀቁን ለችሎቱ አብራርቷል።
ቀሪዎቹ ተጠርጣሪዎች ተስፋሁነኝ ንጉድ ፣ተስፋ ገ/ማርያም ፣ቶማስ ገ/ማረያም እና መስፍን ወርቁ ዛሬ በሶስት ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ የተፈቀደላቸው መሆናቸውም ተመላክቷል።
መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠኝ ጊዜ 1ኛ ተጠርጣሪ ላይ ባደረኩት ምርመራ ለሽብር ወንጀል ማስፈጸሚያ ከ250 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ መሰብሰቡን በማስረጃ አርጋግጫለው ብሏል።
በተጨማሪም ግለሰቡ በሚጠቀምበት ፌስቡክ ገጽ አመጽና በጥብጥ ለማስነሳት ቅስቀሳ ማደረጉን የሚገልጽ የቴክኒክ ማስረጃ ሰብስቤያለሁም ነው ያለው።
2ኛ ተጠርጣሪም በማህበራዊ ድረገጽ ላይ የትግራይ ህዝብ አልቋል ስለዚህ ለጦርነት ተነሱ እያለ ሲቀሰቅስ እንደነበር በማስረጃ ማረጋገጡን ፖሊስ ገልጿል።
4ኛ ተጠርጣሪም ቶማስ ገ/ማረያም ከህወሓት የጸረሰላም ቡድን እና ከኦነግ ሸኔ አመራሮች ጋር በመገናኘት ተልኮ በመቀበል ለወንጀሉ ማስፈጸሚያ የገንዘብ ድጋፍ ሲደረግለት እንደነበር ማስረጃ ማሰባሰቡን የገለጸው መርማሪ ፖሊስ ሌሎችም በተመሳሳይ ተግባር በትብብር መሳተፋቸውን የሚያስረዳ ማስረጃ እንዳለሁም አስረድቷል።
ለተጨማሪ ምርመራ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛልም ነው ያለው ።
1ኛ ተጠርጣሪ ተስፋሁነኝ እኔ በፌስቡክ ለትግራይ ልማት ማህበር ድጋፍ እንዲደረግ ናደም እንዲለግሱም ቀስቅሻለው፣ በመቶ ሺህ ብር ደረጃ በብድር ያለኝ እንጂ በሚሊየን አይደለም ሲል ለችሎቱ አስረድቷል።
ሌሎችም ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም በማለት በዋስ እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ጉዳዩን የተከታተለው ችሎቱ 3ኛና 6ኛ ተጠርጣሪዎችን ላይ ማስረጃ አላገኘሁም በሚል በዋስ ተለቀዋል።
ፍርድቤቱም በቀሪ ተጠርጣሪዎች ላይ አስፈላጊ ማስረጃ አልቀረበም ፣ በተሰጠ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የሰው ማስረጃ በተገቢው አልተሰበሰበም ሲል እያንዳንዳቸው በሶስት ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ አዟል።
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ አባላትም ዋስትናው ተገቢነት የለውም ይግባኝ እንደሚሉ ለጣቢያችን ገልጸዋል።
በታሪክ አዱኛ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል
https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!