ከ33 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ ተያዙ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 29 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአንድ ሳምንት ከ33 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያለው የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ ተያዙ።
በገቢ እና ወጪ ኮንትሮባንድ የተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች ከህዳር 18 እስከ 24 ቀን 2013 ዓ.ም ባሉት ቀናት ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ነው።
ከዚህ ውስጥ 31 ሚሊየን 253 ሺህ 301 ብር የሚገመት ንብረት ወደ ሀገር ለማስገባት ሲሞከር የተያዘ ሲሆን ወደ ውጭ ሲጓጓዙ የተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ግምታዊ ዋጋ 2 ሚሊየን 176 ሺህ 760 ብር መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ የተያዙት በፍተሻ፣ በብርበራ እና በተሽከርካሪ በመከታተል ሲሆን የጉምሩክ ሰራተኞች እና አመራሮች ከፌደራል ፖሊስ አባላት ጋር በቅንጅት መስራት በመቻላቸው መሆኑም ተገልጿል፡፡
ህዝቡን ጥራቱና ደህንነቱ ካልተረጋገጠ ምርት ለመጠበቅና ኢትዮጵያ ከታክስና ቀረጥ ማግኘት የሚገባትን ገቢ እንድታገኝ የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን አመራር፣ ሰራተኞች እና የጸጥታ አካላት ቁርጠኛ ሆነው እየሰሩ መሆኑንም ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።