Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ከተማ ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን ይዞ የተገኘ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 28 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ ሐሰተኛ የደቡብ አፍሪካ የገንዘብ ኖቶችና በተለያዩ የሂሳብ ደብተሮች ላይ ከ184 ሺህ ብር በላይ ይዞ የተገኘ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

ግለሰቡ በአዲስ አበባ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው አውቶብስ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በፓትሮል ስራ ላይ በነበሩ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል አባላት በቁጥጥር መዋሉን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ ጸጥታና ህግ ማስከበር የቀጠና ሁለት አዛዥ ኮማንደር ባደግ ክፍሌ ገልጸዋል፡፡

ህብረተሰቡ ለፖሊስ በሰጠው ጥቆማ መሰረት ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን በሰዓቱ ይዞት በነበረው ሻንጣ ፍተሻ ሲደረግ በርካታ ሐሰተኛ የደቡብ አፍሪካ የገንዘብ ኖቶችና በተለያዩ የሂሳብ ደብተሮች ላይ ከ184 ሺህ ብር በላይ የኢትዮጵያ ገንዘብ ተገኝቶበታል፡፡

ግለሰቡ በፖሊስ ሲጠየቅ ከአማራ ክልል ምዕራብ ጎጀም አካባቢ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱንና ሐሰተኛ የደቡብ አፍሪካ ገንዘቦቹን ከሌላ ሰው በ57 ሺህ የኢትዮጵያ ብር መግዛቱን የተናገረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ እያካሄደበት መሆኑን ኃላፊው መግለፃቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በህጋዊ መንገድ ሰርቶ ህይወትን ማሸነፍና ራሱን መለወጥ እየቻለ በአቋራጭ መንገድ ለመበልፀግ ግለሰቡ የፈጸመው ህገ-ወጥ ድርጊት እንዳስቆጣቸው የገለጹት ኮማንደር ባደግ ክፍሌ ማንኛውም ሰው ከእንደዚህ አይነቱ ተግባር እንዲቆጠብ አሳስበዋል፡፡

ህብረተሰቡ ከጸጥታ ሀይሉ ጎን በመሰለፍ፣ ጥቆማ በመስጠትና መሰል ህገ-ወጥ ተግባራትን በማጋለጥ ረገድ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.