አቶ ኤሊያስ ሽኩር ከአኖካ ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 24 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ክቡር አቶ ኤሊያስ ሽኩር ከአፍሪካ የኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር( አኖካ )ፕሬዚዳንት ሚስተር ሙስጠፋ ባራፍን ጋር ተወያይተዋል።
አቶ ኤሊያስ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ባደረጉት ውይይትም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ስፖርት ልማት እና እድገት ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች መሆኑን እና ወደፊትም ይህን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልፀዋል ፡፡
ኮሚሽነሩ አያይዘውም የአኖካ ጠቅላላ ጉባኤን ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ እድል በመሰጠቱ አመስግነው ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀዋል ፡፡
ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱ የሀገራችን ስፖርት በተለይም የተገነቡትን እና በመገንባት ላይ የሚገኙትን የስፖርት መሠረተ ልማቶች ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነውም ብለዋል ፡፡
ከዚያም ባለፈ የሀገሪቱን ስፖርት ለማስፋፋት እና ለማሳደግ መንግስት ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል ፡፡
የአኖካ ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፋ ባራፍ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የአኖካን ጠቅላላ ጉባኤ ለማስተናገድ ላሳየችው ፍላጎት እና እየተደረገ ላለው ዝግጅት ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀዋል ፡፡
ፕሬዚዳንቱ አክለውም ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ጋር በመተባባር የኦሊምፒዝም ፅንሰ ሀሳብን ለማስፋፋት እና አጠቃላይ ስፖርቱን ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
አኖካም የኢትዮጵያን ስፖርት ለማሳደግ እና ለማስፋፋት ለሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ÷በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የአኖካ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለአደረጉት ሙሉ ድጋፍ የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና አኖካ ከፍተኛ ምስጋና ማቅረባቸውን ገልፀዋል ፡፡
ዶክተር አሸብር አያይዘውም የአኖካ ጠቅላላ ጉባኤ በሚካሄድበት ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ለአደረጉት ከፍተኛ የስፖርት ልማት ድጋፍ እውቅና እና ሽልማት የአኖካ አመራሮች ይዘው መጥተዋል ማለታቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!