በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩት ከፍተኛ መኮንኖች ለ2ኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ሬዲዮ ግንኙነት በማቋረጥ በጦሩ ላይም አሰቃቂ የግድያ ወንጀል፤ የአካል ጉዳትና የጦር መሳሪያ ዝርፊያ እንዲፈፀም አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ 7 ከፍተኛ መኮንኖች እና ሌሎች ከወታደራዊ መኮንኖች ውጪ ያሉ 5 ግለሰቦች ለ2ኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረቡ።
ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ በማድረግ ዛሬ ፍድርድ ቤት ያቀረበው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ባለሙያዎች ናቸወ።
ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበው በቀዳሚ መዝገብ ጉዳያቸው የታየው የመከላከያ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ሜጀር ጄነራል ገብረመድህን ፍቃዱ፣ የመከላከያ ሰራዊት ምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይርዳው ገብረ መድህን፣ የደቡብ ዕዝ ሰው ኃብት ልማት አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ገብረህይወት ሲስኖስ፣ የሰሜን ዕዝ መረጃ ዘርፍ ኃላፊ ብርጋዴር ጀኔራል ኢንሶ ኢጳጆ እራሾ፤ ብርጋዴል ጄኔራል ፍስሃ ገብረስላሴ፣ ኮሌኔል ደሳለኝ አበበ እና ኮሌኔል እያሱ ነጋሽ ናቸው።
ተጠርጣሪዎቹ መንግስትና ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተው መቀመጫውን ትግራይ ክልል ካደረገ የፀረ ሰላም ቡድን ከፍተኛ አመራሮች ተልዕኮ በመቀበል ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሀገር መከላከያ የሰሜን ዕዝ ሬዲዮ ግንኙነት በማቋረጥ ሰራዊቱ እርስ በርስ እንዳይገናኝ በማድረግ በጦሩ ላይም አሰቃቂ የግድያ ወንጀል፤ የአካል ጉዳትና የጦር መሳሪያ ዝርፊያ እንዲፈፀም አድርገዋል ተብለው በመጠርጠራቸው ነው መርማሪ ፖሊስ ምርመራ እያደረገ የሚገኘው።
በተጨማሪም የፌደራል መርማሪ ፖሊስ እንዳመላከተው በሀገር ውስጥና ከውጭ የሚቃጣበትን ጥቃት እንዳይከላከልና የሰሜን ዕዝ ጦር እንዲፈርስ በማድረግ በተቀናጀ መልኩ ኦነግ ሸኔ ከተባለና ከሌሎች የፀረ ሰላም ሃይሎች ጋር በመተባበር በተለያዩ ክልሎችም ሐይማኖትን ሽፋን አድርገው የብሄር ግጭት በማስነሳትም ሀገርን ለመበተን ሲሰሩ እንደነበር መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ ገልጾ ነበር።
መርማሪ ፖሊስ እነዚህ ተጠርጣሪዎች የመከላከያ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ሜጀር ጄነራል ገብረ መድህን ፍቃዱን ጨምሮ ሃገርን በመክዳት ወንጀልና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ለመናድ በማሰብ ወንጀል የተጠረጠሩ ሰባት የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ዛሬ ፍርድ ቤት አቅርቧቸዋል።
ተጠርጣሪዎቹ በፌዴሬል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው ቀርበው ጉዳያቸው ለሁለተኛ ጊዜ የታየው።
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ሁለት የምርመራ ባለሙያዎች ከዚህ በፊት በተሰጣቸው የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ የሰሯቸውን የምርመራ ስራዎችን ለችሎቱ ይፋ አድርገዋል።
በዚህም መሰረት መርማሪ ፖሊስ የስድስት ሰዎች የምስክርነት ቃል ተቀብሎ ከመዝገቡ ጋር ማያያዙን፣ የተጠርጣሪዎችን ቃል መቀበሉን፣ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በተጠርጣሪዎችን ቤት እና ቢሮ ፍተሻ ማደረጉንና በፍተሻውም በርካታ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት ያላቸው የጦር መሳሪያዎችን ማግኘቱን እና በኢግዚቢትነት መያዙን እንዲሁም የተጠርጣሪዎች የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ለሚመለከተው ተቋም ለምርመራ ተልኳል ነው የተባለው።
በተጨማሪም ተጠርጣሪዎች በሃላፊነት በነበሩበት ወቅት ይህን የወንጀል ተግባር ለመፈጸም ከሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ጋር በህቡዕ ስብሰባና ምክክር ሲያደርጉ እንደነበር መረጃ ያገኘና የቪዲዮ ማስረጃም እንዲላክ መጠየቁን መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ አስታውቋል።
መርማሪ ፖሊስ ቀሪ ያላቸውን ማለትም የተጨማሪ የምስክር ቃል መቀበል፣ የሰው ህይወት ያጠፋ ፣ የአካል ጉዳት ያደረሰ፣ በተለያዩ ቦታዎች በርካታ የሃገሪቱ ልማቶችንና ንብረቶች ያወደመ መሆኑ በመጥቀስ ይህን በተመለከተ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ለመስብሰብ፣ ያልተያዙ ግብረ አበሮቻቸውን ለመያዝ፣ የቴክኒክ ማስረጃ ለማስመጣትና ቀሪ ስራ ለመስራት ተጨማሪ ጊዜ ያሰፈልገኛል ሲል ችሎቱን ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው እኛ ለበርካታ ዓመታት ለሃገር ታግለናል፤ ምርመራው በአብዛኛው የተጠናቀቀ መሆኑን ተረድተናል ስለዚህም ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም፤ ዋስትና የፈቀድልን እና ጉዳያችንን በውጭ ሆነን እንከታተል ብለዋል።
እንዲሁም የቤተሰብ አስተዳደሪ ነን የባንክ ሂሳባችን ታግዷል ለቤተሰብ ቀለብ መስጠት አልቻልንም ፍርድ ቤቱ ለቀለብ እንድንሰጥ ይፍቀድልን፤ ከቤተሰብ ምግብ እና አልባሳት ከማስገባት ውጪ ለመነጋገር ይፈቀድልን፤ ክሳቸን በቡድን ነው በተናጠል ይታይልን የሚሉ አቤቱታዎቸን አቅርበዋል።
የጤና እክል አለብን ያሉ ተጠርጣሪዎችም ነበሩ፤ 7ኛ ተጠርጣሪ ኮሌኔል እያሱ ለሃገሬ 30 ዓመት ያለረፍት ታግያለሁ በነዚህ ጊዜያት ሁለት ጊዜ ብቻ ነው ፍቃድ እኳ ያገኘሁት፤ በሃገሬና በህዝቤ ላይ የፈጸምኩት የስነ ምግባር ጉድለት ካለ ልቀጣ፤ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት የለኝም ሲሉ እያነቡ አቤቱታ አቅርበዋል።
ከቤተሰብ ጋር ተማክረን ጠበቃ እንድንወክል ይፈቀድልን ሲሉ ያቀረቡትን አቤቱታ የተቀበለው ችሎቱ ለ2 ደቂቃ በጠበቃ ለማቆም ዙሪያ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተማከሩ ሲሆን፤ አስቀድመው የመክፈል አቅም ስለሌለኝ መንግስት ጠበቃ ያቁምልኝ ሲሉ በሃይማኖታቸው እጃቸውን አንስተው ቃለመሃላ የገቡት 2ኛ ተጠርጣሪ የመከላከያ ሰራዊት ምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይርዳው ገብረ መድህን በድጋሚ ከቤተሰብ ጋር ተማክረው ሃሳባቸውን በመቀየር በግል ጠበቃ አቆማለሁ፤ አስቀድሜ መንግስት ያቁመልኝ ስል የገባሁት ቃለመሃላ ይነሳለኝ ብለዋል።
በጠበቃ የመወከል ህግ መንግስታዊ መብት መሆኑን የችሎቱ ዳኛ ገልጾ ፈቅዶላቸዋል።
የተጠረጠሩበትን ወንጀል ክብደት ውስብስብነት ከግምት በማስገባት ለመርመኛሪ ፖሊስ ተጨማሪ 13 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።
መርማሪ ፖሊስ የተጠርጣሪዎቹን የባንክ ሂሳብ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት መኖሩን እና አለመኖሩን በማጣራት ግንኙነት ከሌለው ለቤተሰብ ቀለብ እንዲጠቀሙ አዟል።
ከቤተሰብ ጋር አንዲገናኙ ያዘዘው የችሎቱ ዳኛ የተናጠል ተሳትፏቸውን እንዲያቀርብ አዟል።
በሌላ በሁለተኛመዝግብ ደግሞ ከወታደራዊ መኮንኖች ውጪ ያሉ 5 ግለሰቦችም ጉዳይ በችሎቱ ታይቷል።
እነዚህ ተጠርጣሪዎች 1ኛ ነጋሲ ንጉስ 2ኛ ገብረተንሳይ አርዓያ 3ኛ ህንጻ ተክለብርሃን 4ኛ ደስታለም ገብረህይወት እና ገብረማርያም ምትኩ ናቸው።
ከ1ኛ አስከ 4ኛ ያሉ ተጠርጣሪዎች ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመያዛቸው ከአዲስ አባባ ፖሊስ ያልቀረቡ ሲሆን፥ በአዳማ ከተማ በቁጥጥር ስር የዋሉት 5ኛ ተጠርጣሪ ገብረማርያም ትኩ ግን በችሎት ቀርበዋል።
መርማሪ ፖሊስም ተጠርጣሪዎቹ መቀሌ ከመሸገው የሽብር ቡድን መረጃ በማቀበል በገንዘብም በመደግፍ ህገ መንግስቱን እና ህገመንግስት ስርአቱን በሃይል ለመናድ ሙከራ ሲያደርጉ በቁጠጥር ስር እንዳዋላቸው ነው የገለጸው።
ተጠርጣሪዎቹ ላይ በርካታ የምርመራ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቅሶ፤ በተለያዩ የሰውና የንብረት ጉዳት በደረሰባቸው የተለያዩ አካባቢዎች የምርመራ ቡድን ልኮ ውጤት እየተጠባበቀ መሆኑ ነው የተጠቀሰው።
ግለሰቦቹ ሲጠቀሙበት የነበሩ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያን ለምርመራ መላኩን ጠቅሷል።
ለተለያዩ ተቋማትና ባንኮች ደብዳቤ ልኮ ውጤት እየተጠባበቀ መሆኑን የገለጸው መርማሪ ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ ተጨማሪ ጊዜ ጠይቋል።
5ኛ ተጠርጣሪው ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም ሲሉ ተቃውመዋል።
መዝገቡን የመረመረው የችሎቱ ዳኛ ወንጀሉ ውስብስብነት አንጻር ተጨማሪ ምርመራ ለፖሊስ ማስፈለጉን ከግምት ውስጥ አስገብቶ የ7 ቀናት ተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ለፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ