ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለፁ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኤድዋርድ ዞለሳ ማካያ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ቀኝ አገዛዝንና የአፓርታይድ ስርዓትን ለመገርሰስ በጋራ የታገሉ የረጅም ዘመናት ወዳጅ ሀገሮች ናቸው።
ሀገራቱ በፀረ አፓርታይድ ትግሉ በጋራ ያስመዘገቡትን የፖለቲካ ድል በኢኮኖሚ ትብብር ዘርፍም መድገም እንዳለባቸው የተናገሩት አቶ ገዱ፥ ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደምትስጥም ገልጸዋል።
ሀገራቱ ቁልፍ በሆኑ የሁለትዮሽ፣ የክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ እያደረጉት ያለውን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸውም ክቡር አቶ ገዱ አሳስበዋል።
በርካታ ኢትዮጵያዊያን በደቡብ አፍሪካ እንደሚኖሩ ያነሱት አቶ ገዱ የዜጎችን ደህንነት በማስከበር በኩል በቅርርብና በትብብር መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
በርካታ ደቡብ አፍሪካዊያን በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረጋቸውን በመግለጽ፤ የባለሀብቶቹ ቁጥር እንዲጨምር አምባሳደሩ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያርጉም አቶ ገዱ በዚህ ወቅት አሳስበዋል።
አምባሳደር ኤድዋርድ ዞለሳ ማካያ በበኩለቸው፥ ታዋቂው የአፍሪካ የጻነነት ታጋይ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ የአፓርታይድን ስርዓት ለመገርሰስ ስልጠና የወሰዱት በኢትዮጵያ መሆኑን በማስታወስ፤ ደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ የምንጊዜም ወዳጅ ናት ብለዋል።
በፓለቲካው ያለው የተሳካ ግንኙነት በኢኮኖሚው ዘርፍ እንዲደገም ደቡብ አፍሪካ እየሰራች ነውም ብለዋል አምባሳደር ኤድዋርድ ዞለሳ ማካያ።
በአምባሳደርነት ቆይታቸውም የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የደቡብ አፍሪካ መንግስት የኢትዮጵያዊያንና የሌሎች የአፍሪካ አገር ዜጎች ደህንነትን
ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑንም አምባሳደሩ አብራርተዋል።
ከዜጎች ደህንነት ጋር በተያያዘ መጤ ጠል ግጭቶችን ለመከላከል ያለመ ኮንፍረንስ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር በዚህ ዓመት በደቡብ አፍሪካ ለማዘጋጀት እቅድ መኖሩን መግለፃቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።