በፍጆታ ምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን ለማስቀረት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2013 (ኤፍቢሲ) ለህብረተሰቡ በሚቀርቡ የፍጆታ ምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን ለማስቀረት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ የህብረት ስራ ማህበራት በሀገር አቀፍ ደረጃ ገበያን ማረጋጋት የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ማህበራቱ ከገጠር እስከ ከተማ ትስስር በመፍጠር አስፈላጊ ምርቶችን ለሸማቹ በበቂ ሁኔታ ያቀርባሉ ነው የተባለው።
የኮቪድ 19፣ ጎርፍ እና በረሀ አንበጣ መከሰት እንዲሁም በሀገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች በተፈጠሩ የሰላም ችግሮች ምክንያት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪዎች መከሰታቸውንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡
ነገር ግን አሁን ላይ ለህብረተሰቡ መቅረብ የሚችል በቂ ምርት መኖሩን ጠቅሰው አቶ ኡስማን ጤፍ እና ሌሎች የዋጋ ንረት የሚታይባቸውን ምርቶች በማህበራቱ ሱቆች በስፋት እንደሚቀርቡ እና ማህበራቱ ምርቶቹን በስፋት ማቅረብ በሚችሉበት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
እንዲሁም ምርቶቹን ወደ ሸማቹ በሚፈለገው ደረጃ መቅረባቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም አስታውቀዋል፡፡
ከፌደራል ጀምሮ እስከ ታች ድረስ ግብረ ሀይል ተቋቁሟል ያሉት አቶ ኡስማን ከእለታዊ ጀምሮ ሳምንታዊ እና የ15 ቀን ተከታታይ ግምገማዎችም ይከናወናሉ ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡም በማህበራቱ የሚቀርቡ ምርቶችን በአግባቡ እንዲጠቀምና ህገወጥ አሰራሮችን ሲመለከት ጥቆማ እንዲያቀርብም ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዙፋን ካሳሁን