20 ኩንታል ‘ካናቢስ’ የተሰኘ አደንዛዥ ዕፅ ሲያጓጉዙ የተገኙ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በሲዳማ ክልል በጤጢቻ ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ከ2 ሺህ ኪሎ ግራም ወይም 20 ኩንታል ‘ካናቢስ’ የተሰኘ አደንዛዥ ዕፅ ሲያጓጉዙ የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎች መያዛቸው ተገለጸ።
በፌዴራል ጉምሩክ ኮሚሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሕግ ተገዢነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢዴሳ ለማ”÷ አደንዛዥ እፁ የተገኘው ትናንት ከሻሸመኔ ወደ ነገሌ ቦረና መስመር ሲጓዝ በነበረ የጭነት ተሽከርካሪ ላይ እንደተጫነ መሆኑ ነው የገለጹት።
ህገ ወጦች አደንዛዥ ዕፁን ከዕይታ ለመሰወር ተሽከርካሪው የግንባታ ብሎኬት የጫነ በማስመሰል ደብቀው ለማሳለፍ ሲሞክሩ በመቆጣጠሪያ ጣቢያ ፈታሾች እና በፌዴራል ፖሊስ አባላት ጥረት ሊደረስባቸው መቻሉን አስታውቀዋል።
አደንዛዥ ዕፁ በኢትዮጵያ ለመጠቀም የተከለከለ ዕፅ በመሆኑ የዋጋ ተመን ባይወጣለትም በጎረቤት ሀገር ሊሸጥ በሚችልበት ዝቅተኛ ዋጋ ተሰልቶ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት እንዳለው አቶ ኢዴሳ አስረድተዋል።
ይህ ‘ካናቢስ’ አደንዛዥ ዕፅ መዳረሻውን በነገሌ ቦረና በኩል ሞያሌ ጠረፍ ያደረገ እንደነበር ገልፀው፤ “አሽከርካሪውና አብሮት የነበረ አንድ ሌላ ተጠርጣሪ ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል” ብለዋል።
አቶ ኢዴሳ ኮሚሽኑ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከክልል የፀጥታ አካላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ጥምረት በመፍጠር በህገ-ወጥ መሳሪያ ዝውውርና ሌሎች ብሄራዊ ሥጋት ሊፈጥሩ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ከወትሮው በተለየ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡