Fana: At a Speed of Life!

የነዳጅ ቅሸባንና ሌሎች በዘርፋ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ዘመናዊ አሠራር ይዘረጋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የነዳጅ ቅሸባንና ሌሎች በዘርፋ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ዘመናዊ አሠራር እንደሚዘረጋ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር፣ ከክልልና ከተማ አስተዳደር የንግድና ኢንዱስትሪ እና ማዕድንና ነዳጅ ቢሮ ኃላፊዎች ጋር  በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ስርዓትን ለማሻሻልና ዘርፋን ለማዘመን የሚያስችል ውይይት  አድርገዋል።

በውይይቱ ወቅት የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ለመቅረፍና ሀገሪቱ ለነዳጅ የምታወጣውን ከፍተኛ በጀት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ነዳጅ የማጓጓዝና የማሰራጨት ሂደቱን ለማሳለጥ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።

የማደያ ቦታዎችን በከተማ ማስተር ፕላን በማካተትና ማደያ ያልተገነባባቸው ቦታዎች በባለሃብቶች እንዲገነቡ በማድረግ የግብይት ስርዓቱን ማዘመን በነዳጅ ማመላለሻ ቦቲዎች ጂ.ፒ.ኤስ እና ሌሎች ዘመናዊ ቴክኖሎጅዎችን በመግጠም ጥብቅ

የቁጥጥር ስርዓት መፍጠር ያስፈልጋል ተብሏል።

በሀገራችን ሁሉም አካባቢዎች ተገንብተው ነዳጅ በማሰራጨት ስራ ላይ ያሉ ማደያዎች ከ900 እንደማይበልጡ እና ሁሉም ማደያዎች ስራቸውን በአግባቡ እንደማይሰሠሩ የገለፁት የንግድ አሰራርና ሬጉላቶሪ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው ናቸው።

ባሳለፍነው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ በተደረገ ቁጥጥርና ፍተሻ አዲስ አበባ ካሏት 120 የነዳጅ ማደያዎች ውስጥ 106 ማደያዎች ስራቸዉን እየሰሩ መሆኑን የታየ ቢሆንም፤ እየሰሩ ካሉ 106 ማደያዎች 55 ብቻ ቤንዚል የሚሸጡ መሆናቸው ተረጋግጧል ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ከፍተኛ የወጭ ምንዛሪ ወጥቶበት ወደ ሀገር የሚገባው የነዳጅ ምርት ለአቅርቦትና ስርጭት ችግር መፈጠር እንደ ምክንያት የሚጠቀሱት ቅሸባ፣ ብክለትና ብክነት እንዲሁም ወደ ጎረቤት ሀገር መልሶ መላክና ሌሎች ህግን ያልተከተሉ አሠራሮች በመኖራቸው ነው ብለዋል።

የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር እና ማዕድንና ነዳጅ ሚንስቴር በቅንጅት አለመስራትና የማዕድንና ነዳጅ ሚንስቴር አደረጃጀት እስከ ክልል፣ ከተማ አስተዳደር መውረድ አለመቻሉ ለችግሩ መፈጠርና ለዘርፉ የአሰራር ክፍተት መኖር ምክንያት መሆኑንም ተቅሰዋል።

የማዕድንና ነዳጅ ሚንስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርካቶ÷ ዘርፉን ለማዘመንና የስርጭት ሂደቱን የሚከታተል በጠቅላይ ሚንስትር የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸዋል።

የክልልና ከተማ አስተዳደር ንግድ፣ ማዕድንና ነዳጅ ቢሮ ኃላፊዎች አደረጃጀት በማስተካከል፣ የነዳጅ ማደያ ቦታዎችን በማስተር ፕላን እንዲካተቱ ለካቢኔያቸው በማስወሰን እስከ ጥር 30 2012 ዓ.ም ለተቋቋመው ኮሚቴ ሪፖርት እንዲያደርጉ ማሳሰባቸውን ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.