ከ2 ሚሊየን ብር በላይ የታክስ ማጭበርበር ወንጀል የፈፀሙ ተከሳሾች በእስራት ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከ2 ሚሊየን ብር በላይ የታክስ ማጭበርበር ወንጀል የፈፀሙ ተከሳሾች በእስራት መቀጣታቸውን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።
1ኛ ተከሳሸ ሊባኖስ ተክለስላሴ፣ 2ኛ ተከሳሽ ዘውዴ ብርሀኔ እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ ያዕቆብ ይስሀቅ፥ የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 96 በአዋጅ ቁጥር 693/2003 አንቀጽ 97 እና የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/94 49 በመተላለፍ ግብር አለመክፈል ወንጀል ነው የተከሰሱት።
1ኛ ተከሳሽ በአዲስ ክተማ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 02 ኤም ጂ 15 በተመዘገበ የንግድ አድራሻ ላይ ከ2003 እስከ 2004 ዓ.ም የግብር ዘመን ካገኙት ገቢ ላይ ለመንግስት መክፈል የነበረባቸውን 2 ሚሊየን 724 ሺህ 858 ብር ከ20 ሳንቲም ባለመክፈል።
እንዲሁም በ2ኛ ክስ ከ2002 እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜያት ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አሳውቀው ሊከፍሉ የሚገባቸውን የተጨማሪ እሴት ታክስ 4 ሚሊየን 133 ሺህ 55 ብር ከ14 ሳንቲም አለመክፈላቸው ተጠቅሷል።
በተጨማሪም በ3ኛ እና 4ኛ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የገቢ ግብር አዋጅ በመተላለፍ በየካ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 19 በ2 ተከሳሽ ስም በተመዘገበ የንግድ አድራሻ አስመጪ የንግድ ዘርፍ ፈቃድ በማውጣት ከ2003 እስከ 2004 ዓ.ም የግብር ዘመን ካገኙት ገቢ ላይ 723 ሺህ 976 ብር ከ58 ሳንቲም ለመንግስት ባለመክፈላቸው በግብረ አበርነት ወንጀል መፈጸማቸው በክሱ ተጠቅሷል።
በ5ኛ እና 6ኛ ክስ ላይ ደግሞ 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 02 ኤም ጂ 3/15፥ በ2ኛ ተከሳሽ በተመዘገበ የንግድ አድራሻ የጽህፈት መሳሪያዎች የንግድ ፍቃድ በማውጣት በ2004 ዓ.ም የግብር ዘመን 67 ሺህ 944 ብር ከ48 ሳንቲም ግብር ባለመክፈል።
እንዲሁም ለመንግስት መክፈል የሚገባቸውን 20 ሺህ 298 ብር ተጨማሪ እሴት ታክስ ባለመክፈል በግብረ አበርነት በፈፀሙት የግብርና ታክስ ማጭበርበር ወንጀል ተከሰው ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል።
ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾች በፈፀሙት ወንጀል ተጠያቂ መሆናቸውን የሚያሳይ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል::
የፌዴራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት የግራ ቀኙን ተመልክቶ፥ 1ኛ ተከሳሽ በ8 አመት ከ6 ወር እና 350 ሺህ ብር እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ በ3 አመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።