Fana: At a Speed of Life!

ሀገር የካደውን የህወሓት የጥፋት ቡድን የሚያወግዝ ሰልፍ በተለያዩ አካባቢዎች ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ህዳር 7 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሀገር የካደውን የህወሓት የጥፋት ቡድን የሚያወግዝ ሰልፍ በተለያዩ አካባቢዎች ተካሄደ፡፡

በዚህም በጋምቤላ፣ በቡሌ ሆራ፣ በሆሳዕና ከተሞች የህወሓት ጽንፈኛ ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ የፈፀመውን ጥቃት የሚያወግዙ ሰልፎች ተካሄደዋል።

የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች የህወሓት ጁንታ እያካሄደ ያለውን ሀገር የማፍረስ ዓላማ ለማስቆም እና ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ የመከላከያ ሰራዊት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ ጠቁመው ከሰራዊቱ ጎን በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ተስፋ የቆረጠ የጥፋት ቡድን በመሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች ባሰማራቸው ቡድኖች ጥቃት ሊፈጽም ስለሚችል የጋምቤላ ክልል ህዝብ ከፀጥታ አካሉ ጋር በመሆን አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ አስገንዝበዋል፡፡

በድጋፍ ሰልፉ ማጠናቀቂያ ላይ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የደም ልገሳ መርሃ ግብር ተከናውኗል፡፡

በተመሳሳይ ዜናም በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ጉጂ ዞን የቡሌ ሆራ ከተማ ነዋሪዎች እና የቡሌ ሆራ ወረዳ ነዋሪዎች በዛሬው ዕለት በቡሌ ሆራ ከተማ ባደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ ፅንፈኛው የሕወሓት ቡድን በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ ያደረሰውን ጥቃት እንደሚያወግዙ ገልጸዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ከድጋፍ ሰልፉ ባሻገር ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ200 በላይ ሰንጋዎች እና ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ብር ድጋፍ በማድረግ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች የሕወሓት ቡድን የፈፀመውን የሀገር ክህደት የሚያወግዝ ሕዝባዊ ሰልፍ በሐዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ አካሂደዋል።

አረመኔው የጥፋት ቡድን ሀገር ለማፍረስ የሚንቀሳቀስ ጠላት መሆኑን በማውገዝ መንግሥት እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ እንደሚደግፉ የሰልፉ ተሳታፊዎች አስታውቀዋል።

የሰልፉ ተሳታፊዎች ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡

የቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲም በትግራይ የህግ ማስከበር ዘመቻ እያካሄደ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት ግምታቸው 680 ሺህ ብር የሆኑ 200 ፍየሎች እና የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.