በአፋር ክልል የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህወሓት ቡድን በመከላከያ ላይ የፈጸመውን ጥቃት አወገዙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህወሓት ቡድን በሃገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት አጥብቀው እንደሚያግዙ ገለጹ።
ፓርቲዎቹ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሠመራ ከተማ ዛሬ ባካሄዱት የምክክር መድረክ እንዳስታወቁት መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየወሰደ ያለው እርምጃ ሁሉም ዜጋ ሊደግፈው ይገባል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የአፋር ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢሴ አደን የህወሓት ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው የእብሪት ጥቃት ዛሬም እንደትናንቱ ሁሉን በበላይነት ለመምራት ያለውን ፍላጎት በህዝብ ላይ ለመጫን የተደረገ ሙከራ ነው ብለዋል።
ድርጊቱ የሀገርን ህልውና እና የህዝብን ሰላም አደጋ ላይ ለመጣል የተቃጣ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት የህግ የበላይነትና የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር ተገዶ ወደ እርምጃ መግባቱን አውስተው የፖለቲካ ሃይሎች ከመንግስት ጋር ተቀናጀተን መስራት የሚገባን ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህንን በመረዳት የክልሉ ብሎም የሀገሪቱ ሰላም እንዲረጋገጥ መላ አባላቶቻቸውን በማስተባበር የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በምክክር መድረኩ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ባለአምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በመውጣት መረሃ ግብራቸውን ማጠናቀቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።