ምክር ቤቱ የተሰጠውን ኃላፊነት በተሻለ መልኩ ለመወጣት ሪፎርም ሊያደርግ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግስቱ የተሰጠውን ኃላፊነት በተሻለ መልኩ ለመወጣት የሚያስችለውን አቅም ለመፍጠር አጠቃላይ ሪፎርም ለማድረግ በሒደት ላይ መሆኑን ገለጸ።
ምክር ቤቱ አሁን ባለው ሁኔታ ሚናውን ለመወጣት በሚያስችለው ቁመና ላይ የማይገኝ በመሆኑ ተቋማዊ ሪፎርም ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ ገልጸዋል።
ሪፎርሙ አራት መሰረታዊ የትኩረት አቅጣጫዎች ማለትም ሕብረ ብሔራዊ ሃገራዊ አንድነትና ዘላቂ ሰላም መገንባት፣ ውጤታማ የፊሲካል ሽግግር፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ማረጋገጥ፣ የሕገ መንግስት የበላይነትን እና ሕገ መንግስታዊነትን ማረጋገጥ እንዲሁም ተቋማዊ የማስፈጻም አቅም ግንባታዎች እንደሚገኙበትም አፈ ጉባኤው አስረድተዋል፡፡
ሪፎርም ማድረግ የሚያስችለው ጥናት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚካሄድ ሲሆን፥ በአራቱ መሰረታዊ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ አተኩሮ ምክር ቤቱን ያጠናክረዋል ተብሎ ይጠበቃልም ነው ያሉት።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አጥኚ ቡድን መነሻ ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን፥ ከጥናቶቹ አንዱ ‘ልዩ ዓላማ ያላቸው የበጀት ድጎማ ጥራትና ስርጭት ዳሰሳ’ የሕገ መንግስት የበላይነትንና ሕገ መንግስታዊነትን ማረጋገጥ ላይ ያተኩራል።
ጥናቱ የበጀት ድጎማ ስልት ክልሎችን ፍትሓዊ በሆነ መልኩ ለመጥቀም በቀጣይ በምን መልኩ እንደሚከናወን አጠቃላይ አቅጣጫን የሚያመለክት ይሆናል።
ሌላው የሚካሄደው የሪፎርም አጋዥ ጥናት ‘በክልሎች መካከል የሚደረገውን የመሰረተ ልማት ዝርጋታን’ የሚዳስስ ሲሆን፥ መሰረተ ልማት ለኢኮኖሚ ዘርፍ ውጤታማነት አቻ የማይገኝለት ዘርፍ መሆኑን በቀረበ መነሻ ጥናት ተጠቅሷል፡፡
በክልሎች መካከል የሚደረገው የመሰረተ ልማት ስርጭት ፍትሃዊነት ማዕከል በማድረግ የማህበረሰብ እና የፖለቲካ ብልጽግናን እውን የሚያደርግ በአጠቃላይ ሀገር መንግስት ግንባታን የሚያግዝ መሆን ባለበት መልኩ እንዲሆንም አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተጨማሪም ሕብረ ብሔራዊነትና ዘላቂ ሰላም ላይ አተኩሮ ስለሚካሄደው ጥናትና የተቋሙን የማስፈጸም አቅም አስመልክቶ ስለሚካሄደው ጥናት መነሻ ሪፖርት ቀርቧል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደ ሃና በበኩላቸው ጥናቱ ምክር ቤቱ በሚፈልገው መልኩ ይካሄዳል ብለዋል።
የጥናቶቹ መነሻውና መድረሻ ሕገ መንግስቱ ለምክር ቤቱ በሰጠው ስልጣን መሰረት ያደረገ እንደሚሆንም ገልጸዋል።
አጠቃላይ ጥናቱን በሁለት ወራት ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ እንደሚሰራ ዩኒቨርሲቲው መግለፁን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።