የተለያዩ ተቋማትና የስራ ሃላፊዎች በክብር ዶክተር ሎሬት አርቲስት ለማ ጉያ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በአንጋፋው ሰዓሊ ሻምበል የክብር ዶክተር ሎሬት አርቲስት ለማ ጉያ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል።
ለቤተሰባቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን ተመኝቷል።
አርቲስት ለማ ጉያ ለየት ባለ የአሳሳል ጥበባቸው ላለፉት 65 ዓመታት ከ10 ሺህ በላይ ሥዕሎችን በፍየል ቆዳ ላይ በመሳል በዓለም ዙሪያ ባሉ ታላላቅ መሪዎች ሳይቀር አድናቆትን የተቸሩ የኢትዮጵያ የጥበብ ምልክት እንደነበሩ ስራዎቻቸው ምስክር ናቸው ብሏል።
ለዚህም ታሪክ ለዘላለም ይዘክራቸዋል ነው ያለው ሚኒስቴሩ።
በተያያዘም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በክብር ዶክተር ሎሬት አርቲስት ለማ ጉያ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።
በክብር ዶክተር ሎሬት አርቲስት ለማ ጉያ ህልፈተ ህይወት የተሰማኝን ሃዘን ለመግለጽ እወዳለሁ ያሉት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ለቤተሰቦቻቸው እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን እመኛለሁ ማለታቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።