በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የሚመጣ ማንኛውንም ኃይል ለመመከት ዝግጁ ነን– በመከላከያ ሰራዊት የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ዋና አዛዥ
አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመከላከያ ሰራዊት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚመጣ ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ኃይልን ለመመከት ዝግጁ መሆኑን የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ሹማ አብደታ ተናገሩ።
ሰራዊቱ በማንኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች ተንቀሳቅሶ ሀገርንና ህዝብን የመጠበቅ ህገ-መንግስታዊ ስልጣኑን የሚያስቆመው አካል እንደሌለም ገልጿል።
በሀገር መከላከያ ሰራዊት የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሹማ አብደታ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ቆይታ አድርገዋል።
ሰራዊቱ በአሁኑ ወቅት ከስነ-ምግባር ጀምሮ የቴክኒክ፣ የትጥቅ፣ የአቅምና ሌሎች አጋዥ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በሚገባ መጠቀም የሚችል፣ በማንኛውም ስፍራ ፈጥኖ ደርሶ ተልዕኮውን መወጣትና ማንኛውንም ጠላት መመከት የሚችልበት ጠንካራ ቁመና ላይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ግድቡ ከመጀመሩም ሆነ ውሃ ከመሞላቱ በፊት የተለያዩ ማስፈራሪያዎች ይሰነዘሩ እንደነበርና ሰራዊቱ ይህንን በመገንዘብ ምንጊዜም በተጠንቀቅ የቆመ ነው ብለዋል።
የልዩ ዘመቻዎች ኃይል በልዩ ኮማንዶ፣ በባህር ጠላቂ ሃይል፣ በአየር ወለድና መሰል አደረጃጀቶች የተደራጀና ማንኛውም ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ መሰናክል ሳይወስነው ግዳጁን የሚወጣ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሰራዊቱ በተለይ አሁን ካላው የፖለቲካ ሁኔታም ይሁን የተፈጥሮ አደጋዎች ጋር ተያይዞ የሀገርን ሰላም፣ የሰው ህይወትና ንብረት ለመጠበቅ በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች ተንቀሳቅሶ ይሰራል ብለዋል።
” የፖለቲካ ጉዳይ የፖለቲከኞች ነው “ያሉት ሜጀር ጀኔራሉ ሰራዊቱ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ስራውን ለመስራት የሚያስቆመው አካል የለም ሲሉ ተናግረዋል።
“የመከላከያ ሰራዊት የአንድ ክልል ወይም የግለሰብ አይደለም” ያሉት ዋና አዛዡ ዓላማው የአገር ህልውና እንዲቀጥል፣ ህዝቦች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ማድረግ እስከሆነ ድረስ ሁሉም የኔ ነው ብሎ መደገፍና ከጎኑ መቆም አለበት ብለዋል።
ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ መከላከያ እንደማይገባ አስታውሰው ከዚህ ያለፈ ችግር ሲኖር ግን መከላከያ ቁንጮና የመጨረሻው መፍትሄ ነው በማለት ገልፀዋል።