በቻምፒየንስ ሊጉ ሪያል ማድሪድ ሲሸነፍ ባየርሙኒክ እና ሊቨርፑል ድል ቀንቷቸዋል
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎች በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ተደርገዋል።
ከምድብ አንድ እስከ አራት በሚገኙ ቡድኖች መካከል በተደረጉ ጨዋታዎች ያልተጠበቁ ውጤቶችም ተመዝግበዋል።
በምድብ አንድ ሎኮሞቲቭ ሞስኮን ያስተናገደው ሳልዝበርግ ጨዋታውን ሁለት አቻ ሲያጠናቅቅ ዞቦዝላይ እና ጁኑዞቪች ለሳልዝበርግ እንዲሁም ሎፔዝ እና ሊሳኮቪች ለሎኮሞቲቭ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።
አሊያንዝ አሬና ላይ በተካሄደው የምድቡ ሌላኛ ጨዋታ ባየር ሙኒክ አትሌቲኮ ማድሪድን 4 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፎታል።
ኮማን (ሁለት)፣ ጎርትዝካ እና ቶሊሶ የድል ጎሎቹ ባለቤት ናቸው።
በምድብ ሁለት በተደረገ ጨዋታ ደግሞ ሪያል ማድሪድ በሜዳው በሻክታር ዶኔስክ የ3 ለ 2 ሽንፈት አጋጥሞታል።
በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በርካታ ተጫዋቹችን ያጣው ሻክታር በቻምፒየንስ ሊጉ የአንበሳ ድርሻ ያለውን ማድሪድ በሜዳው በማርቲንስ እና ሶሎሞን እንዲሁም ራፋኤል ቫራን በራሱ መረብ ላይ ባስቆጠራት ጎል አሸንፎታል።
ሉካ ሞድሪች ቪኒሺየስ ጁኒዬር ደግሞ ለባለሜዳዎቹ የማስተዛዘኛዎቹን ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።
በምድቡ ሌላኛ ጨዋታ የጀርመኑን ቦሩሲያ ሞንቼግላድባህን ያስተናገደው ኢንተር ሚላን ጨዋታውን ሁለት አቻ በሆነ ውጤት አጠናቋል፤ ሉካኩ ለኢንተር ሚላን ጎሎቹን ሲያስቆጥር ቤንሴባይኒ እና ሆፍማን ደግሞ ለእንግዳው ቡድን ጎሎቹን በስማቸው አስመዝግበዋል።
በምድብ ሶስት ደግሞ ማንቼስተር ሲቲ ፖርቶን 3 ለ 1 ሲያሸንፍ አጉዌሮ፣ ጉንዶጋን እና ቶሬስ ለማንቼስተር ሲቲ እንዲሁም ዲያዝ ለፖርቶ ጎሎቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።
በምድቡ ሌላኛ ጨዋታ ደግሞ ኦሊምፒያኮስ በሃሰን ማህጉብ ብቸኛ ጎል ማርሴይን 1 ለ 0 አሸንፎታል።
በምድብ አራት ወደ ሆላንድ ያቀናው ሊቨርፑል ታግሊያፊኮ በራሱ መረብ ላይ ባስቆጠራት ጎል አያክስ አምስተርዳምን 1 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል።
አታላንታ ደግሞ ሚዲቲላንድን ዛፓታ፣ ጎሜዝ፣ ሙሪዬል እና ኢሊቺቺ ባስቆሯቸው ጎሎች ከሜዳው ውጭ 4 ለ 0 በማሸነፍ ባለድል ሆኗል።