የፊት ገጽታን ጨምሮ ያየችውን ነገር የማታስታውሰው ሩሲያዊት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የ29 አመቷ ሩሲያዊት በጣም ያልተለመደ ግን አደገኛ ሊባል የሚችል የጤና ሁኔታ አጋጥሟታል፡፡
ሌና አሽ የተባለችው ወጣት የራሷን ጨምሮ የሰዎችን የፊት ገጽታ ማስታወስ በማያስችል ፕሮሶፓግኖዚያ የተባለና ብዙም ያልተለመደው አጋጣሚ ተጠቂ ናት፡፡
ሌና አሽ በአጋጣሚው መጠቃቷን ያወቀችው ባለፈው አመት ሲሆን ከማወቋ በፊት ራሷን ከሌሎች ሰዎች የዘገየች እንደሆነች እንድታስብ ተገዳ ነበር፡፡
የፊት ገጽታን ጨምሮ ያየችውን ነገር በሙሉ የመርሳትና ያለማስታወስ ችግር ከልጅነቷ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፤ ስላጋጠማት ችግር ለቤተሰቦቿ ብታሳውቅም መፍትሄን ማግኘት አልቻለችም ነበር፡፡
ወጣቷ ከሰዎች ጋር በትምገናኝበት ወቅት የሰዎችን ማንነት በደንብ መለየት ብትችልም ከተለያየች በኋላ አብሯት የነበረን ሰው ማንነትም ሆነ የፊት ገጽታ ማስታወስም አትችልም፡፡
የሌና ችግር የሰው ልጅ አዕምሮ ያየውንና የመዘገበውን ነገር የሚያስታውስበት ሂደት አለመኖሩ ነው፡፡
በሆነ አጋጣሚ ከሰው ጋር ተገናኝታ ከተለያየች በኋላ የዛን ሰው ማንነትም ሆነ የፊት ገጽታ በጭራሽ ማስታወስ አትችልም፡፡
“ሌላው ቀርቶ በስራ አጋጣሚ ትናንት ያገኘኋቸውን ደንበኞች ዛሬ በሌላ አጋጣሚ ሳገኛቸው በጭራሽ አላስታውሳቸውም” ትላለች፤ በዚህ ሳቢያ በርካቶች እንደተቀየሟትም ትገልጻለች፡፡
“ዛሬ ያየሁትን ፊልም ነገም እንደ አዲስ እመለከተዋለሁ”” የምትለው ሌና ምናልባት በቀጣይ 10 አመታት ውስጥ ሁሉንም ነገር እረሳለሁ” በሚል ከባድ ፍራቻ ውስጥ ስለመሆኗ እና ነገ ምን ሊፈጠር እንደሚችል እንደማታውቅም ትናገራለች፡፡
ሁሉም ነገር ከቁጥጥሯ ውጭ በመሆኑ ሳቢያም የህክምና ባለሙያዎችን ቢያንስ የማስታወስ ችሎታየ ይስተካከል ዘንድ አንድ ነገር አድርጉ ስትልም ትማጸናለች፡፡
የሌና ችግር ህክምናም ሆነ መፍትሄ የሌለው ሲሆን በዚህ አይነቱ አጋጣሚ የሚጠቁ ሰዎችም እምብዛም ስለመሆናቸው የዘርፍ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ፡፡
ምንጭ፡- ኦዲቲ ሴንትራል