በቻምፒየንስ ሊጉ ጁቬንቱስ፣ ማንቼስተር እና ባርሴሎና ድል ቀንቷቸዋል
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 11 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ትናንት ምሽት በተለያዩ ከተሞች ተካሄደዋል፡፡
ከምድብ አምስት እስከ ስምንት በሚገኙ ቡድኖች መካከል በተደረገው ጨዋታ ታላላቆቹ ቡድኖች ድል ቀንቷቸዋል፡፡
በምድብ አምስት የተደረጉ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ፥ ቼልሲ ከሲቪያ ያለምንም ጎል አቻ ተለያይተዋል፡፡
በሌላኛው የምድቡ ጨዋታ ደግሞ ሬኔስ ከክራስኖዳር ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ ተጠናቋል፡፡
በምድብ ስድስት ደግሞ ዜኒት በሜዳው በክለብ ብሩዥ 2 ለ 1 ሲሸነፍ ላዚዮ ደግሞ ቦሩሲያ ዶርትመንድን 3 ለ 1 አሸንፏል፡፡
ኢሞቢሌ፣ ሂትዝ እና አክፕሮ የላዚዮን የድል ጎሎች ሲያስቆጥሩ ሃላንድ ደግሞ ለዶርትመንድ የማስተዛዘኛዋን ጎል አስቆጥሯል፡፡
በምድብ ሰባት ወደ ዩክሬን ያቀናው ጁቬንቱስ ዳይናሞኬቭን 2 ለ 0 ሲያሸንፍ ሞራታ የድል ጎሎቹን ማስቆጠር ችሏል፡፡
በምድቡ ሌላኛው ጨዋታ በሜዳው የሃንጋሪውን ክለብ ኤፍ ቲ ሲን ያስተናገደው ባርሴሎና 5 ለ 1 አሸንፏል፡፡
ሊዮኔል ሜሲ(2)፣ አንሱ ፋቲ፣ ኮቲንሆ እና ደምበሌ የድል ጎሎችን ለባርሴሎና ሲያስቆጥሩ፤ ካራቲን ለእንግዳው ቡድን ማስተዛዘኛዋን በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል፡፡
በምድብ ስምንት ወደ ፓሪስ ያቀናው ማንቼስተር ዩናይትድ በብሩኖ ፈርናንዴዝ እና ራሽፎርድ ጎሎች ፒ ኤስ ጂን 2 ለ 1 አሸንፏል፡፡
ለ ፒ ኤስ ጂ አንቶኒ ማርሻል በራሱ መረብ ላይ አስቆጥሯል፡፡
በምድቡ ሌላ ጨዋታ ሌፕዚግ ኢስታንቡል ባሻክሼርን 2 ለ 0 አሸንፎታል፤ አንጄሊኖ ደግሞ የድል ጎሎቹ ባለቤት ነው፡፡