ችግር ፈቺ የሞባይል አፕሊኬሽን እና ኮዲንግ ስልጠናዎች ለሴት ተማሪዎች መስጠት የሚያስችል ስምምነት ተደረገ
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 15፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ)ሴት ተማሪዎች በትርፍ ጊዜያቸው ችግር ፈቺ የሞባይል አፕሊኬሽን እና ኮዲንግ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ የሚያግዝ ስምምነት መፈረሙን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ስምምነቱ የተፈረመውም ከኮኖቬሽን ኢንተርፕረንርሺፕ ዲቨሎፕመንት ከተባለ ድርጅት ጋር መሆኑ ተነግሯል፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ÷ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ሲመደቡላቸው ተቀብሎ ከማስተማር ጎን ለጎን በአከባቢያቸው ካሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጋር ትስስር በመፍጠር ፣ተማሪዎችን በቀጣይ የዩኒቨርስቲ ቆይታቸው ውጤታማ የሚያደርጉና በሳይንስ ዘርፉም ፍላጎት እንዲያድርባቸው የሚያግዙ ስራዎችን ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች በአይሲቲ ዘርፍ ያላቸውን አቅርቦት ለስልጠናው በማመቻቸትና መምህራንንም በማሳተፍ ሴት ተማሪዎች በሞባይል አፕሊኬሽን እና ኮዲንግ ላይ የሚሰጣቸውን ስልጠና ይደግፋሉ፡፡
ይህ ስምምነት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዩኒቨርሲቲዎች ባሉበት አከባቢ የማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጡ ለሚሰራው ስራ እና የሳይንስ ባህል ግንባታ ላይ የሰጠው ትኩረት አንድ አካል ነው ብለዋል፡፡
የኮኖቬሽን ኢንተርፕረንርሺፕ ዲቨሎፕመንት በኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ገብረሚካኤል÷ ሴት ተማሪዎች በሳይንስ ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑን አንስተዋል።
ፕሮጀክቱ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ጀምሮ ሳይንስ ውስጥ እንዲገቡ የሚያግዙ ስልጠናዎችን በማመቻቸት በሳይንስ ዘርፍ የሚመረቁ ሴት ተማሪዎችን ቁጥር ከፍ የማድረግ ዓላማ አለው ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱን እውን ለማደረግ የዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ ወሳኝ መሆኑንና በፕሮግራሙ ታቅፈው ስልጠናውን ተከታትለው ጥሩ ውጤት ለሚያስመዘግቡ ሴት ተማሪዎችም የነፃ ትምህርት እድሎችን እንደሚያመመቻቹ ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱን ለመጀመሪያ ጊዜ በተመረጡ ዩኒቨርስቲዎች እንደሚጀምሩና ከዚያም በመነሳት በሁሉም ዩኒቨርስቲዎች የማስፋፋት እቅድ እንዳላቸውም አስተባባሪው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ተማሪዎች የአይ ሲ ቲ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ ማመቻቸቱን አስታውቀዋል፡፡
በተለይም ዲጂታል ሊትሬሲ በሚል የክረምት የስልጠና ፕሮግራም በሁሉም ዩኒቨርስቲዎች በማካሄድ የተለያዩ የማህበረሰብ አካላት መሰረታዊ የዲጂታል ክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።
በቀጣይም የዚህ አይነት ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሮፌሰር አፈወርቅ መግለጻቸውን ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡