የድሬዳዋ አስተዳደር ከቻይናው ሲ.ሲ.ኢ.ሲ.ሲ ጋር የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ስምምነት ተፈራረመ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከቻይናው ሲሲ.ኢ.ሲሲ (CCECC) ኩባንያ ጋር የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ስምምነት ተፈራረመ።
ስምምነቱንም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ ቡህ እና የሲሲ.ኢ.ሲሲ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጉዎ ቾንግፌንግ ትናንት በድሬዳዋ ከተማ ተፈራርመዋል።
በትናንትናው እለት የተፈረመው ስምምነት በከተማዋ የቻይናው ሲሲ.ኢ.ሲሲ (CCECC) በመጀመሪያ ዙር በ370 ሄክታር መሬት ላይ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት የሚያስችለው መሆኑን የድሬደዋ ከንቲባ ዕህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
የቻይናው ሲሲ.ኢ.ሲሲ በድሬዳዋ መልካጀብዱ አካበቢ 1 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የራሱን የኢንዱስትሪ ፓርክ ገንብቶ የቻይና በተለይም የድሬዳዋ እህት ከተማ ከሆነችው የኩንሻን ከተማ ባለሀብቶችን ለማምጣት አቅዶ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።
አሁን የተደረሰው የ370 ሄክታር መሬት ስምምነት የመጀመሪያ ዙር እንደሆነ በፊርማ ስነስርዓቱ ወቅት ተገልጿል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ የመሬት ርክክቡ ተጠናቆ የግንባታ ስራው እንደሚጀመር በሚጠበቀው የኢንዱስትሪ ፓርክ ከግንባታው ጀምሮ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል።
የአካባቢው ነዋሪዎችን ጨምሮ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ለስራው መቀላጠፍ የበኩላቸውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ወቅት ጥሪ ቀርቧል።
ከዚህ በፊት ምክትል ከንቲባ አህመድ ቡህ የድሬዳዋ እህት ከተማ በሆነችው ኩንሻን ከተማ ባደረጉት ጉብኝት ሁለቱ ከተሞች በቀጣይ የሚኖራቸውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነት በተለይም የሲሲ.ኢ.ሲ.ሲ ኩባንያ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታን ለማስጀመር እና ኢንቨስትመንትን በተጠናከረ ሁኔታ ለማስቀጠል የሚያስችል ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።