በኢንዶኔዢያ በመኪና አደጋ የ24 ሰዎች ህይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 14፣2012(ኤ.ቢ.ሲ) በኢንዶኔዢያ በህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪ ላይ በደረሰ አደጋ የ24 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ።
በህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪው አደጋው ያጋጠመው በኢንዶኖዢያዋ ዴንፖ ቴንጋህ ግዛት ሱማትራ ፓጋር አላም ከተማ መሆኑ ተነግሯል።
የፓጋር አላም ከተማ ፓሊስ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት አደጋው ያጋጠመው የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካርው 150 ሜትር ጥልቅት ወዳለው ሸለቆ በመግባቱ ነው ብለዋል።
በዚህ አደጋ ህይወታቸው ካለፈው 24 ሰዎች በተጨማሪ 13 ሰዎች የአካል ጉዳት አጋጥሟቸዋል ተብሏል።
ተሽከርካሪው ወደ ሸለቆው ከመግባቱ በፊት ከመንገድ ዳር ከሚገኝ የኮንክሪት መሰናክል ጋር መጋጨቱ ታውቋል።
አንዳንድ ሰዎች አሁንም ድረስ በአውቶቡሱ ውስጥ ተጣብቀው እንደሚገኙ እና ተጎጂዎችን ከአደጋው የማንሳት ተግባር መቀጠሉ ተጠቁሟል።
ህይወታቸው ያለፈ እና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ወደ ፓጋላራላም ቤስማህ ሆስፒታል ተወስደዋል ተብሏል።
በኢንዶኔዥያ በደካማ የደህንነት መስፈርቶች እና የመሰረተ ልማት ችግሮች ምክንያት የመንገድ አደጋዎች የተለመዱ መሆኑ ተገልጿል።
ምንጭ፡- አልጀዚራ