የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለመግታት የሚያግዝ መመሪያ ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስቴር ኮቪድ-19 በመከላከል ዜጎች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበትን መመሪያ ይፋ አደረገ።
በኢትዮጵያ መጋቢት 2012 ዓ.ም የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ የሚያደርሰው ጉዳት እየጨመረ መጥቷል።
በአሁኑ ወቅት 79 ሺህ ያህል ዜጎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፣ ከ1ሺህ 200 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። በጽኑ ሕሙማን ክፍልም 285 ሰዎች ይገኛሉ።
የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በዓዋጅ የተሰጣቸውን ሥልጣን በመጠቀም በጋራ መመሪያ አዘጋጅተዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የመመሪያውን ይዘት በሚመለከት ዛሬ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
መንግሥት ኮቪድ-19 በአገሪቱ መከሰቱን ተከትሎ የስርጭቱን መጠን ለመቀነስና ለመግታት የኮቪድ መከላከል ግብረ ኃይልን ከማቋቋም በተጨማሪ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ታውጆ እንደነበር አስታውሰዋል።
የዓዋጁን መነሳት ተከትሎ ህብረተሰቡ መዘናጋት ውስጥ ከመግባቱ ባሻገር የስርጭት ምጣኔው በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በመስፋፋት ስጋት መፍጠሩን ገልጸዋል።
በዚህም ኮቪድ-19ን በመከላከል ረገድ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እያደረገ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው መመሪያውን እንዲተገብር ሚኒስትሯ አሳስበዋል።
መመሪያው ኮቪድ 19 እንዳለበት በምርመራ የተረጋገጠ ማንኛውም ሰው ወደ አገር መግባት፣ቫይረሱን ሊተላለፍ በሚችልበት ሁኔታ ከሰዎች ጋር ንኪኪ ማድረግ፣ለሰላምታም ሆነ ለሌላ ዓላማ እጅ ለእጅ መጨባበጥና መተቃቀፍ ፈጽሞ ይከለክላል።
ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ ህጻናት በስተቀር የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ጭምብል) ሳይጠቀሙ በማንኛውም ቦታ ላይ መንቀሳቀስ በሕግ እንደሚያስቀጣም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በክፍት ገበያዎች፣በትራንስፖርት መሳፈሪያ ቦታዎች፣ሕዝባዊ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ስፍራዎች ሌሎች መሰል ቦታዎች ላይ ሁለት የአዋቂ እርምጃ ርቀት መጠበቅና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል) መጠቀም ግዴታ መሆኑን ይደነግጋል።
ማንኛውም የግልም ሆነ የመንግሥት የትምህርት ተቋማት ትምህርት የሚጀመርበትን ትክክለኛ ወቅትና መመሪያ ሳይደርሳቸው ትምህርት መጀመር እንደማይችሉ ዶክተር ሊያ አስታውቀዋል።
የህጻናት ማቆያ ማዕከላትም አገልግሎት የሚሰጡበት መመሪያ እስኪወጣላቸው ዝግ ሆነው እንደሚቆዩ ገልጸዋል።
የመንግሥትም ሆነ የግል የሥራ ተቋማት ሰራተኞቻቸው ወረርሽኙን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራትን መከታተልና ማስተግበር እንደሚጠበቅባቸው ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል።
ምን ዓይነት የበሽታውን ምልክት የማያሳይ የኮቪድ-19 ታማሚ በቤት ውስጥ የሚደረግለት ሕክምና እንደሚቀጥል ገልጸው፣ታካሚው ቢያንስ ለ14 ቀናት ከማህበረሰቡ ራሱን አግልሎ መቆየት ግዴታ ነው ብለዋል።
የኳረንቲንና የድንበር ላይ ጤና ቁጥጥርን በሚመለከት ከትራንዚት መንገደኛ በስተቀር ከ10 ዓመት ዕድሜ በላይ የሆነ ማንኛውም ተጓዥ ከመጣበት አገር ነጻ መሆኑን የሚያሳይ የምርመራ ውጤት ማሳየት ይጠበቅበታል።
በቀጣይም በአውሮፕላን ማረፊያው ምርመራ ከተደረገለት በኋላም አድራሻውን በማስመዝገብ በቤቱ ለሰባት ቀናት ለይቶ የመቆየት ግዴታ እንደተጣለበት ገልጸዋል።
ከመጣበት አገር ፖዘቲቭ የሆነ ውጤት ይዞ የሚመጣ መንገደኛ ኢትዮጵያ ውስጥ መግባት እንደማይችልም ዶክተር ሊያ አመልክተዋል።
በየብስ የሚገባ መንገደኛ ከበሽታው ነጻ መሆኑን የሚያረጋግጥበት የምርመራ ውጤት ቢኖረውም፤ ለሰባት ቀናት በቤቱ መቆየት ግዴታ እንዳለበት አብራርተዋል።
የቀብር ሥነ-ሥርዓት፣ የሰርግና የቤት ውስጥ ማህበራዊ ዝግጅቶች ከ50 ሰዎች ባልበለጠ እንደሚከወኑና የጥንቃቄ መርሆዎች እንደሚተገበሩ መመሪያው ያስገድዳል።
የሰዎችን በአንድ ቦታ መሰባሰብ ለማስቀረት ስብሰባዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደግፈው ይካሄዳሉ ያሉት ሚኒስትሯ፣ አስገዳጅ ከሆነ ከ50 ሰዎች ባልበለጠና ርቀትን በጠበቀ መልኩ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ማካሄድ ይቻላል ብለዋል።
አገልግሎት የሚሰጥባቸው ካፌዎች፣ባርና ሬስቶራንቶች፣መጠጥ ቤቶች፣የመዝናኛና የመጫወቻ ስፍራዎች በጠረጴዛ ሶስት ሰዎችን ብቻ ማስተናገድና ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
ሲኒማ ቤቶች፣ትያትር ቤቶችና የሥዕል ጋለሪዎች ያላቸውን ቦታ ከግምት ውስጥ በማስገባት አንድ አራተኛ ተመልካቾችን ብቻ በመለየትና በሽታውን መከላከል መርሆዎችን በማስተግበር ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የስርጭቱ ምጣኔ እየታየ በድጋሚ ሌላ መመሪያ እስኪወጣ ድረስ ከማረሚያ ቤት በስተቀር በማዕከላትና ማገገሚያ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን መጠየቅ ክልክል መሆኑን ዶክተር ሊያ አብራርተዋል።
ይሁን እንጂ ማረሚያ ቤቶች ላይ የጥየቃ አገልግሎቱ ርቀትን በጠበቀና ምንም ንኪኪና ግንኙነት በሌለው መልኩ ማድረግ ይችላሉም ነው የተባለው።
ስፖርታዊ ውድድሮች በተለይም የእግር ኳስ፣የእጅ ኳስ፣ቅርጫት ኳስ፣ቴኒስና አትሌቲክስ ታዳሚ በሌለበት መከናወን እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ዜጎች መመሪያዎችን በመተግበርና በማስተግበር ወረርሽኙን በመከላከል ድርሻቸውን እንዲወጡ ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል፡፡